በድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ የተመራው ከአስተዳደሩ ከአራቱም የገጠር ክላስተር የተውጣጣ ልዑክ ወደ ማእከላዊ ኢትዮጵያ ስልጤ ዞን በማምራት በአገር አቀፍ ደረጃ በገጠር ኮሪደር ልማት በተሞክሮነት የሚጠቀሰውን የሁልባራግ ወረዳ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ በአስተዳደሩ ኢኮኖሚ ፋይዳቸው የጎላ የሆነና የተዳከሙ ኮሪደሮችን ማነቃቃት በሚያሰችል መልኩ በከተማው ክፍል በተለያዩ ስፍራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
እንደ ከተማው ክፍል ሁሉ በአራቱም የገጠር ክላስተሮች የገጠር ኮሪደር ልማት ለማከናወን መታቀዱን ገልፀው ለዚህም ይረዳ ዘንድ ስራዉን ቀድሞ ተግባራዊ ከተደረገበት የስልጤ ዞን ልምድ መውሰድ መቻሉን አብራርተዋል።
በልምድ ልውውጡም በገጠር ግብርናን እና የከብት እርባታን በማዘመን እንዲሁም የግልና የቤተሰብ ንፅህናን ጠብቆ ምቹና ያማራ አካባቢን መፍጠር የሚቻልበትን መንገድ ትምህርት ለመቅሰም መቻሉን ጠቅሰዋል።በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን ከድሬደዋ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ እንደሚደረግ ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጰያ በስልጤ ዞን የሁልባራግ ወረዳ ዋና አስተዳደ አቶ ሻፊ ሀምደላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የገጠር ኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቭ ተከትሎ ስራው መጀመሩን ጠቅሰው ማህበረሰቡን በማሳተፍ በአጭር ጊዜ ለሰርቶ ማሳያነት ጭምር የሚውል የገጠር የኮሪደር ልማት ስራ መከናወኑን በቀጣይም ከዚህ በመነሳት ሁለት መቶ ቤቶችን በተመሳሳይ ለማልማት መታቀዱን ጠቁመዋል።
በጉብኝቱ ከተካተቱ ባለድርሻ አካላት ውስጥ የድሬደዋ ግብርና ውሀ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሓላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ እንዲሁም የስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው በልምድ ልውውጡ ከሚመሩት ዘርፎች ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በቀጣይ በአስተዳደሩ ለሚከናወነው የገጠር ኮሪደር ልማት ሊያበረክቱት የሚችሉትን አስተዋጽኦ በሚመለከት ተሞክሮ ማግኝታቸውን ተናግረዋል።


