በየዓመቱ የሚከበረውን የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ምክንያት በማድረግ የድሬዳዋ ነዋሪዎች እና የአስተዳደሩ አመራሮች የበዓሉ ተሳታፊ እንግዶችን የሚቀበሉበት መርሀግብር በአመት ሁለት ጊዜ የሚሰናዱ ሲሆን ለበዓሉ ተሳታፊዎች በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች የማረፊያ ድንኳን በመጣልና ማረፊያ በማዘጋጀት፥ የእንግዶችን ሰላም፣ደህንነት ከነዋሪው ጋር ተቀናጅተው ይጠብቃሉ።
በፍቅር በሰላም ተምሳሌት ትንሿ ኢትዮጵያ ተብላ በምትታወቀው ድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች ተጠቅመው ወደ ከተማዋ ለሚመጡ የሀይማኖት አባቶች፣ምዕመናን፣ የበዓሉ ተሳታፊዎችን ከአቀባበል ጀምሮ በአሉን በሰላም አክብረው እስኪመለሱ ድረስ የድሬዳዋ አስተዳደር ከአስተዳደሩ የፀጥታ ኃይላትና ከምስራቅ ኢትዮጵያ የጋራ የፀጥታ ጥምር ግብረሃይል ጋር በመቀናጀት የሰላም እና የደህንነት ስራውን በሚገባ ለመወጣት ዝግጅት መደረጉን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ለፀጥታ የጋራ ግብር ሀይል የላቀ የግዳጅ አፈፃፀም ሽልማትና እውቅና መርሀግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንንግር አረጋግጠዋል።
በከተማዋ ላይ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች እንግዶችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ለማስተናገድ በሆቴሎች፣በንግድ ዘርፍ ፣ በትራንስፖርት ዘርፍ የተቀናጀ ህጉን በጠበቀ መልኩ ለማገልገል ድሬዳዋ ተዘጋጅታለች ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል።
የቁሉቢ ገብርኤል ንግስ በዓልን ለማክበር ከተለያዩ የሀገራችን ከተሞች የሚመጡ ምዕመናን እና የበአሉ ተሳታፊዎችን በፍቅር ለማስተናገድ ዝግጅት መጠናቀቁን ከንቲባ ከድር ተናግረዋል።
እንግዶች እገረ መንገዳቸውን በድሬዳዋ የተሰሩትን የልማትና የመሠረተ ልማት ግንባታ የድሬደዋ የኮሪደር ልማት መዳረሻዎችን የድሬ የባቡር ሽርሽር የድሬዳዋ ቱሪዝም መዳረሻዎችን በመጎብኘት የቆይታ ጊዜያቸውን የተሻለ በማድረግ ማሳለፍ እንዳለባቸው የድሬደዋ ከንቲባው ጠቁመዋል።
ድሬደዋ የነፃ ንግድ ቀጠና ማዕከል የኢንዱስትሪ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መናገሻ ከተማ መሆኑዋን ያስታወሱት ከንቲባ ከድር የንግድ፣ኢኮኖሚ፣ ኮሪደር ለውጭ ንግድ ቅርበት ስላላት ከለውጡ ማግስት ድሬደዋ በማንሰራራት ላይ ያለች ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።
ለዚህም በርካታ ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ እያለሙ የሚገኙ ሲሆን ሌሎችም ባለሀብቶች፥በፍቅርና በሰላሟ የምትታወቀው ትንሿ ኢትዮጵያ ተብላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ወደ ተሰየመችው ድሬዳዋ አስተዳደር ቢመጡ አስተዳደሩ በፈለጉት ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተናገረዋል።


