የታህሳስ 19 የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል በስኬት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።
በቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከውጭ ከሚመጡ የእምነቱ ተከታዮች በተጨማሪ ቱሪስቶችና ሌሎች እንግዶች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።
የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊና የአካባቢው ጊዜያዊ የጸጥታ ግብረ ሃይል ሰብሳቢ ረዳት ኮሚሽነር ናስር መሐመድ፤ በበዓሉ ወቅት ወንጀል እንዳይፈጸም ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከዝግጅቱ ውስጥ የፀጥታ አካላትና ሕግ አስከባሪዎች በዓሉ በሚከበርበትና በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡን በማሳተፍ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ጥበቃ ስምሪት እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።
በበዓሉ ወቅት በወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ በማድረግ ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት እንዲያስችልም ጊዜያዊ ፍርድ ቤት በገዳሙ አካባቢ መቋቋሙንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያዎች እንደተቋቋሙ የገለጹት ረዳት ኮሚሽነር ናስር፤ የበዓሉ ታዳሚዎች ወደ በዓሉ ስፍራ ሲጓዙ ንብረቶቻቸው በጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በአካባቢው ዳገት፣ ቁልቁለት እና ጠመዝማዛ መንገድ የሚበዛበት እንዲሁም ወቅቱ ጉም በመሆኑ አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህግና የፀጥታ አካላት፣የትራንስፖርት ቁጥጥር ሰራተኞችና ድጋፍ ሰጪ ወጣቶች የሚያስተላልፉትን መልዕክት አክብረው እንዲያሽከረክሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከታህሳስ 18 እስከ ታህሳስ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ቀናት ከጨለንቆ እስከ ቀርሳ ከተማ ባሉት ከተሞች ዋና መንገድ ላይ ከባድ ተሽከርካሪ ማለፍ ክልክል መሆኑንም ረዳት ኮሚሽነር ናስር ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።


