በድሬዳዋ አስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የንግድ፣ የኢንደስትሪ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ስራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ስራዎች ይከናወናሉ” የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ም/ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ።

”በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ሲሰጥ በነበረው የስልጠና ማጠቃለያ ላይ ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሠጡት የስራ አቅጣጫዎች መሠረት በተመረጡ ዘርፎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ የ100 ቀን እቅድ በድሬዳዋ አስተዳደር ተዘጋጅቶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን ፤ በአስተዳደሩ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮና ተጠሪ ተቋማት እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባና የኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ገለፃ ሰተዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር እስከ መጋቢት 10/2018 ዓ.ም ድረስ የሚፈፀመውን የ100 ቀን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ በአስተዳደሩ ኢንደስትሪና ኢንቨርትመንት ቢሮና ተጠሪ ተቋማት በኩል በርካታ ተግባራትን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ስራ እንደተገባ ም/ከንቲባው ጠቅሰዋል።

የኑሮ ውድነቱን በማቅለሉ ረገድ ለማህበረሰቡ ምርቶችን በበቂ ደረጃ ለማቅረብ የፋብሪካና የግብርና ምርቶችን የመጨመር እንዲሁም የሌማት ቱሩፋት ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ እየተሰሩ እንደሚገኙ ም/ከንቲባው ገልፀዋል።

በተያያዘም የሰንበት ገበያዎችን ከማጠናከር ጎን ለጎን የቁጥጥር ስራዎች ማለትም የዋጋ ንረቱን ሊያባብሱ የሚችሉ ህገ-ወጥ ደላሎችን ከንግድ ሰንሰለቱ የማሶጣትና አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የማገናኘት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ም/ከንቲባ ሀርቢ ተናግረዋል።

ኮትሮባንድን ዜሮ ለማድረግ እንደመስተዳደር ኮሚቴ ተዋቅሮ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ም/ከንቲባ ሀርቢ ጠቁመዋል።

የዳሬዳዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅትን የቱሪስት መዳረሻ ለማረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ሀርቢ ተቋሙ ከ125 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ በመሆኑ በቅርስነት እንዲያዝ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሚገኙና በአጠቃላይ ተቋሙን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

ም/ከንቲባው አያይዘውም በአስተዳደሩ በከፍተኛ ደረጃ የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪዝም እያደገ መምጣቱን ጠቁመው በቀጣይም ይህንን የማስቀጠል ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በከተማው ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መኖራቸውንና በቀጣይም በርካታ ዘመናዊና ቅንጡ ሆቴሎች ወደገበያው እንደሚቀላቀሉ አቶ ሀርቢ አመላክተዋል።

በአስተዳደሩ የሽያጭ ማዕከል ለማደራጀትም የቦታ ልየታና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ም/ከንቲባው ጠቁመው፤ ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ጋር ተያይዞ የቡና ማቀነባበሪያን በመገንባትና ወደ ውጪ ለመላክ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የእስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘም በነፃ የንግድ ቀጠናና በመልካ መካከል የሚገኝ 10 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካና የኤሌክትሪክ መኪናዎች ማምረቻ ለመገንባት

የቅድመዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አቶ ሀርቢ ተናግረዋል።

ለአምራች ኢንደስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የሚያብራሩት ምክትል ከንቲባ ሀርቢ “በኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በድሬዳዋ ምርትና ምርታማነትን መጨመር፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት ፣ ኤክስፖርትን የማሳደግና ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የመፍጠር ስራ እነተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንደ አስተዳደሩ በ 2018 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ የተመረቁ 11ዱ ፋብሪካዎችን ሳይጨምር 369 ማኒፋክቸሪንግ ኢንደስትሪዎች ያሉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሀ 38ቱ ከፍተኛ 71 መካከለኛና 260 አነስተኛ መሆናቸውን በመጠቆም ፋብሪካዎቹ ጨርቃጨርቅና ምግብና ምግብ ነክ ምርቶችን በስፋት የሚያመርቱ በመሆኑ የኑሮ ውድነቱን ለማቅለል የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ም/ከንቲባው በቀጣይ አዳዲስ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ የማስገባት ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁ ሲሆን በአጠቃላይም በድሬዳዋ አስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የንግድ፣ የኢንደስትሪ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ስራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ስራዎች ይከናወናሉ እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በመጨረሻም በአስተዳደሩ በኮሪደር ልማት፣ በፋይዳ መታወቂያና በኢትዮ ኮደስ ስልጠና ላይ እየተሰሩ የሚገኙ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ም/ከንቲባው ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *