የነዳጅ ቅሸባን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የኦቶሜሽን ሥርዓት እየዘረጋን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት በነዳጅ ላይ የሚያደርገውን ከፍተኛ ድጎማ አሁንም መቀጠሉን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በምክር ቤት ተገኝተው እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በየቀኑ ክለሳ ቢደረግበትም፤ ኢትዮጵያ ግን ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ የዋጋ ማሻሻያ ያደረገችው ሰባት ጊዜ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት ይህን ከፍተኛ ድጎማ የሚያደርገው እና ወደብ ካላቸው ሀገራት በታች በሆነ ዋጋ የሚያቀርበው፣ የዋጋ ጭማሪው በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ድጎማ ለሕገ-ወጥ ተግባራት መጋለጡን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ነዳጅን ወደ ጎረቤት ሀገራት የማሸሽ (ኮንትሮባንድ) ተግባር በሰፊው እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ነዳጅ ማደያ የሚመስሉ ሕገ-ወጥ ቦታዎች እየተስፋፉ መሆኑንም አክለዋል ተናግረዋል።

ይህንን ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በዘላቂነት ለመግታት፣ በቅርቡ በኦቶሜሽን የተደገፈ የቁጥጥር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ጠቁመዋል።

ይህ አዲስ ሥርዓት ሲዘረጋ እያንዳንዱ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ያለበትን ቦታ፣ የት እንደተራገፈ እና ነዳጁ ለታለመለት ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስት በቅርቡ ወደ ጂቡቲ ባደረጉት ጉዞም፣ በዚህ ዘርፍ የታዩ ክፍተቶችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎች ላይ ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

EBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *