” በድሬዳዋ አስተዳደር ከለውጡ ማግስት ወዲህ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በገፅታ ግንባታ ስራዎች አበረታች ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ማህበረሰቡም ከውጤቱ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል”:-የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር

በድሬዳዋ አስተዳደር ከለውጡ ማግስት ወዲህ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በገፅታ ግንባታ ስራዎች አበረታች ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ማህበረሰቡም ከውጤቱ ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ ድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” ! በሚል መሪ ቃል በብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተዘጋጀ የግማሽ አመት ማጠቃለያ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚህም በመርሃ-ግብሩ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በድሬዳዋ አስተዳደር በ2018 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ውስጥ በመንግስትና በፓርቲ ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን አኩሪ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለ ገልፀው፤ በተለይም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የክረምት በጎ ፍቃድና የአርንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭን ጨምሮ በርካታ ፕሮግራሞች በአስተዳደሩ ተግባራዊ ለማድረግ ከአስተዳደሩ ነዋሪዎች ጋር ስራዎች በርብርብ መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ ስራዎች በአጠቃላይ በአዲስ የተገነቡና እድሳት የተከናወነላቸው ከአራት መቶ ሰማኒያ በላይ ቤቶች ለማህበረሰቡ የተላለፉ ሲሆን አጠቃላይ ቤቶቹም በገንዘብ ሲተመኑ ከመቶ ስልሳ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመቱ ከንቲባ ከድር ጠቁመዋል።

ክቡር ከንቲባ ከድር አያይዘውም በአስተዳደሩ ከዘጠና አምስት ሺ በላይ የሚደርሱ ወጣቶችን በክረምትና በበጋ ወራት በተለያዩ ስራዎች ማሳተፍ መቻሉን ጠቁመው፤ በዓላት እና አዲስ ዓመት ከመግባት ጋር ተያይዞ ከሰማኒያ ሰባት ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማእድ ማጋራት የተቻለ ሲሆን ድጋፉም በገንዘብ ሲተመን ከስልሳ አምስት ሚሊዮን ብር የሚበልጥ መሆኑ ተጠቁሟል።

በአስተዳደሩ ፍጥነትና ፈጠራ የታከለበት ስራዎችን ለመፈጸም ያስችል ዘንድ የመቶ ቀናት እቅድ ታቅዶ ለተግባራዊነቱ የነቃ ተሳትፎ እየተደረገ መሆኑን ከንቲባ ከድር ተናግረው በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው ፓርቲው በ 2018 በጀት አመት የመጀመሪያው ግማሽ አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩትን በርካታ ስኬታማ ውጤቶች ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

እንደ ድሬደዋ አስተዳደርም በብልፅግና ፓርቲ የድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም ዘርፎች አበረታች የሆኑ አፈጻጸሞችን ማስመዝገብ የተቻለበት መሆኑን አቶ ኢብራሂም ገልፀዋል።

አቶ ኢብራሂም አያይዘውም ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገቡ ውጤቶች ለቀጣይ ስኬት መስፈንጠሪያ በመሆናቸው አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በጳጉሜ ቀናት ንቅናቄ፣ በትምህርት ለትውልድና በከተማ ልማት በአስተዳደሩ አበረታች ስራዎች እንደተሰሩ አቶ ኢብራሂም ጠቅሰው የአስተዳደሩ ማህበራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት እንዲሻሻል ፓርቲው በትኩረት መንቀሳቀሱንም አመላክተዋል።

7ተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በመጪው ግንቦት ወር የሚከናወን ሲሆን ምርጫው በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው በመሆኑ ምርጫው ዲሞራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ተዓማኒ እና ነፃ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በማስቻሉ ረገድ የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ከወዲሁ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን ሲሉ አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *