ኢትዮጵያ ስማርት የፖሊስ አገልግሎትን በማስጀመር በአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ናት – ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

ኢትዮጵያ የሰው አልባ (ስማርት) ፖሊስ አገልግሎትን በማስጀመር በአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር መሆኗን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሰው አልባ ፖሊስ አገልግሎት ወይም ስማርት ፖሊስ አገልግሎት በይፋ አስጀምረዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ ይህን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ አገልግሎት የሕግ ማስከበር ስራን ወደ ዲጂታል በማሸጋገር ህብረተሰቡ ያለምንም እንግልትና የሰው ንክኪ የወንጀል፣ የትራፊክ አደጋ እና ሌሎች አቤቱታዎችን በቀላሉ ለፖሊስ የሚያደርስበትን ሥርዓት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

እንዲህ ዓይነቱ ዘመናዊና ስማርት የፖሊስ አገልግሎት በዓለም ላይ በጥቂት የአውሮፓና የእስያ ሀገራት ብቻ የሚገኝ መሆኑን ጠቀሰው፣ ኢትዮጵያም ይህንን አገልግሎት በመጀመር በአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ የፖሊስን የሥራ ቅልጥፍና ከመጨመሩ ባለፈ በህብረተሰቡ ዘንድ ግልጽነትና እምነትን የሚያሰፍን መሆኑንም ነው የገለፁት።

ተገልጋዮች ጉዳያቸውን ካስመዘገቡ በኋላ የሚሰጣቸውን የፋይል ቁጥር በመጠቀም፣ እስከ ፍርድ ቤት ያለውን ሂደት በቅርበት መከታተል እንደሚችሉ ኮሚሽነር ጀነራሉ አብራርተዋል።

በቀጣይም ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር አገልግሎቱን በሞባይል ስልክ በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበት ሂደት እየተከናወነ መሆኑንና ቱሪስቶችም ፓስፖርታቸውን በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *