የ2018 ዓ/ም የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር በአስተዳደሩ የወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን አስተባባሪነት በበጎ ፈቃድ ተግባራቶች የላቀ ተሳትፎ ለነበራቸው ግለሰቦች፣ባለሀብቶች ፣ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣የወጣትና ሴቶች አደረጃጀቶች የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል ።
በመርሃ ግብሩም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ተገኝተው በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጽት፤ ወጣቶች ለሀገሪቱ ብሎም ለአስተዳደሩ በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካ ዘርፍ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲመዘገብ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የመደመር መንግስት መገለጫ የሆነው በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ ኢንሼቲቭ የተጀመረው ሰው ተኮር አገልግሎቶች በማህበራዊ ዘርፍ ለተመዘገበው ስኬት ለሀገሪቱ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነዉ ብለዋል።
ይህን ተከትሎም በአስተዳደሩ በ14 ዘርፎች እና በ47 ጠቋሚዎች(ማሳያዎች) ከ95ሺ በላይ ወጣቶችን በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በማሳተፍ 173 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
የወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ መሀመድም በበኩላቸው በአስተዳደሩ በበበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የህብረተሰብ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአረንጓዴ አሻራ፣በማዕድ ማጋራት፣በደም ልገሳ፣በጽዳት ዘመቻ፣በአረጋውያን ቤት ጥገና በሌሎች ልዮ ልዩ
ዘርፎች ስኬታማ ስራዎች መሠራታቸውን አንስተው በተለይም ለአቅመ ደካማ አረጋውያን 322 አዳዲስ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች መተላለፉን ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የላቀ ተሳትፎ ለነበራቸው ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና ማህበራት የዋንጫ እና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።


