“ድሬዳዋ የነፃ ንግድ ቀጠና እና የምስራቁ የሀገራችን ኢንዱስትሪ መዕከል ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የእድገት ግስጋሴዋን የሚመጥን የውሃና ሳንቴሽን አገልግሎት በእጅጉ ያስፈልጋታል”:- የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር

በድሬዳዋ አስተዳደር ከአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን( 1. 3 ቢሊዮን) ብር በላይ በሆነ ወጭ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ ማጣሪያና ማስወገጃ የኦፕሬሽንና ጥገና ፕሮጀክት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በዚህም በመርሃ-ግብሩ የተገኙት ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር የግንባታ ፕሮጀክቱ የአስተዳደሩን የፍሳሽ አያያዝና አወጋገድ ስርዓትን በላቀ ደረጃ የሚያሻሽል መሆኑን ተናግረው፤ ድሬዳዋ የነፃ ንግድ ቀጠና እና የምስራቁ የሀገራችን ኢንዱስትሪ መዓከል ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የእድገት ግስጋሴዋን የሚመጥን የውሃና ሳንቴሽን አገልግሎት መስጠት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

ክቡር ከንቲባ አያይዘውም በሁለተኛው የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በተሰራ ስራ በድሬዳዋ አስተዳደር የሚታየውን የመጸዳጃ ቤቶችን ችግር ማቃለል እንደተቻለ ገልፀው፤ የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነውና ከአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን( 1. 3 ቢሊዮን) ብር በላይ በሆነ ወጭ በዛሬው ዕለት የመሰረት ድንጋይ የሚጣልለት የፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት ድሬዳዋን ለኑሮ ምቹ፣ ተስማሚ እና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው አመላክተዋል።

ለግንባታ ፕሮጀክቱ አስተዳደሩ 13 ሄክታር የግንባታ መሬት የማዘጋጀት፤ ከአካባቢው ለሚነሱ የልማት ተነሺዎች ከሃያ ስምንት ሚሊዮን (28,000,000.00) ብር በላይ የካሳ ክፍያና የምትክ መሬት ቦታን በማዘጋጀት ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እና እገዛ ማድረጉን ክቡር ከንቲባ ከድር ጠቁመው፤ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተለያየ ጊዜ ለአሰተዳደሩ በውሃና ፍሳሽ ዘርፍ ሲያደርጋቸው ከነበሩ ድጋፍና አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለዚህ ፕሮጀክት መጀመር ላበረከተው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የውኃ እና ኢነርጂ ሚንስቴር ሚንስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው የፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት ለማህበረሰቡ ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ ለአካባቢውን ለዜጎች ከፍተኛ የስራ እድልን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም የአስተዳደሩን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን የውሃና ሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጠናቅቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በግንባታ ሂደቱ የሚሳተፉ ሁሉ በቁርጠኝነትና በሙሉ አቅም በመስራት ፕሮጀክቱን ከግብ ማድረስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ይህ ፕሮጀክት በመቀሌ፣ በአዳማ ፣ በድሬዳዋ፣ በሀዋሳና በባህርዳር የሚተገበር መሆኑንም ክቡር ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ እንደ አስተዳደር የመጀመሪያና ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ስራ አስከያጅ ኢንጂነር መሀመድ ሙሴ ሲሆኑ ድሬን ንፁህና ለእይታ ማራኪ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *