ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀዋሳ እና አካባቢው ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት፤ በሁሉም መስክ የተቀናጀ ሥራ በመሥራት ኢትዮጵያን የምግብ ቅርጫት የማድረግ ህልማችንን እናሳካለን ሲሉ ገልጸዋል።
ከሀዋሳ እስከ ሞጆ የተገነባው የፍጥነት መንገድ ለፍራፍሬ ምርት፣ ለቱሪስት ፍሰት እና ለኢንዱስትሪ ግብዓቶች ዝውውር ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በመንገዱ ግራና ቀኝ ያለውን ለም መሬት በመጠቀም፣ አሁን የተጀመረው የፍራፍሬ ልማት መላውን አካባቢ እንዲያካልል በትጋት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
“የአንድ ዘርፍ ስኬት ብቻውን የሀገርን ችግር አይፈታም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ግብርናን በዕውቀት መምራት፣ ኢንዱስትሪን በገበያ ተኮር መንገድ ማስፋፋት፣ ከተሞችን ማዘመን እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ለኢትዮጵያ ህልውና እና ሰላም ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የጀመርናቸው የሌማት ትሩፋት እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ሲሰናሰሉ የምናልማትን ኢትዮጵያ ለመገንባት በእጅጉ ያግዛሉ በማለትም ጥረቶች ሲቀናጁ ሁለንተናዊ ለውጥ እንደሚመጣ ጠቅሰዋል።
ለታየው ውጤት የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች ሊመሰገኑ እንደሚገባ ገልጸው፣ ማኅበረሰቡ እነዚህን የልማት ሥራዎች በመጠበቅ እና በማስፋፋት፣ ኢትዮጵያን የምግብ ቅርጫት የማድረግ ህልምን ለማሳካት በጋራ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በመሠረተ ልማት ዘርፎች የታዩ ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።


