ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና ብልጽግና ዋስትና የሚሆን ዘመናዊ ሠራዊት ገንብታለች – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በልዩ ዘመቻዎች 65ኛ ዓመት በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ዋነኛ ራዕይ ለትውልድ የሚሸጋገር ስትራቴጂያዊ ተቋም መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የልማት እሳቤ ውኃን እንደ ልማት እና ሕይወት ምንጭ ማየት መጀመሩን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ አስተሳሰብ በወታደራዊው ዘርፍም ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣቱን አስረድተዋል።

ቀደም ሲል በየብስ እና በተራራ ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረው ሥልጠና አሁን ወደ ባሕር መሸጋገሩን ጠቁመው፣ ይህም ኢትዮጵያ በባሕር ላይ የሚጋረጡ የሽብር ስጋቶችን ለመከላከል እና ለቀጠናው ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራትም አለኝታ ለመሆን በቂ ዝግጅት ማድረጓን በመጥቀስ፣ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል በድሮን እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ ብቃት ያለው ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ በቴክኖሎጂ የዳበረ እና በየብስም ሆነ በባሕር ውጤታማ የሆነው ተቋም መገንባቱ ለምሥራቅ አፍሪካም ትልቅ የምሥራች መሆኑንም ነው የገለጹት።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በመላው አፍሪካ ሰላም እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚተጋ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ሽብርን በማስቀረት ለጋራ ብልጽግና ከወንድም ሕዝቦች ጋር በቅንጅት እንደምትሠራም አረጋግጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *