ውጊያን የሚያስቀር አየር ወለድ፦ የኢትዮጵያ አዲሱ የጥንካሬ መገለጫ::

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛው የምስረታ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሀገሪቱ የመከላከያ አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን አብስረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገነባችው ልዩ ኃይል ተራ ተዋጊ ብቻ ሳይሆን፣ ውጊያን የሚያስቀር እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ውጊያን በአጭር የሚቀጭ ብቃት ያለው ነው።

እነዚህ ባለሁለት ክንፍ ተምዘግዛጊ አየር ወለዶች በአንደኛው ክንፋቸው የጸና ዓላማን፣ በሌላኛው ደግሞ የማይናወጥ ዲሲፕሊንን አንግበው ከአየር የሚወርዱ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የዚህ ኃይል ዋነኛ ተልዕኮ የሀገርን ሰላም ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፣ ጠላት ጦርነትን እንዳያስብ የሚያደርግ የመከላከያ አቅም (Deterrence power) መፍጠር እንደሆነም በሰፊው አብራርተዋል።

መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለው ይህ የ”ኤሊት ፎርስ” ግንባታ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ከመጠበቅ ባለፈ ለቀጣናዊ ሰላምም ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

አክለውም ይህ ኃይል ወንድም የሆኑ የጎረቤት ሕዝቦችን በመደገፍ ሽብርን ለማስቀረት እና በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የጋራ ልማት እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ የገነባችው ልዩ ኃይል የጦርነት ወሬን የሚዘጋ እና የሰላም ዋስትና ሆኖ የሚያገለግል የሀገር ኩራት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአጽንኦት ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *