መጋቢት 24 የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ በሀገር ውስጥ ልማት ብቻ ሳይወሰን፣ በዲፕሎማሲው መስክም አስደማሚ ድሎችን አምጥቷል።
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) “መደመር” እሳቤ ሀገራችንን ከገለልተኝነት ወደ ንቁ ተሳትፎና መሪነት አሸጋግሯታል። ባለፉት ስምንት ዓመታት ያገኘናቸው ዲፕሎማሲያዊ እውቅናዎችና አጋርነቶች የአመራሩ ብስለትና የጸና ሀገራዊ ፍቅር ውጤቶች ናቸው።
በለውጡ ዓመታት ኢትዮጵያ የነበረባትን የዲፕሎማሲ ከበባ በመስበርና ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበሩ ረገድ እመርታ የታየባቸው ስኬቶችን አስመዝግባለች።
ኢትዮጲያ ከጎሮቤት ጋር ተዋዳ ከአለም ጋርም ተጋምዳ ትኖር ዘንድ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተናገሩ ሲሆን ቃልንም በተግባር በመፈፀም በርካታ ድሎችን መጎናፀፍ ተችሏል።
ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ አቅጣጫች የመንግሥት ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ጽኑ ቁርጠኝነት መገለጫ ነው። ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ በህጋዊ መንገድ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ጀምሮ በተለያየ መንገድ ከሀገር የወጡና ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን ወደ እናት ሀገራቸው ለመመለስ የተከናወኑ ተግባራት መንግሥት ለሕዝቡ ያለውን አለኝታነት ያሳዩና በዜጎች ዘንድ የላቀ ብሔራዊ ኩራትና መተማመንን የፈጠሩ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው።
ከለውጡ አመታት ጀምሮ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት፣ በኢኮኖሚ ግንባታ፣ በፖለቲካዊ ተፅዕኖ ፈጠራ እና በዕውቀት ሽግግር ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል።
የመደመር መንግስት የዲያስፖራው ማህበረሰብ በተለይም በገንዘብ ልውውጥ (Remittance)፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በሰብአዊ እርዳታ እና በዲፕሎማሲያዊ ዘመቻዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በአገር ግንባታ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥራል።
የለውጡ መንግሥት ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የመስጠት መርሕን በመከተል በቀጣናው ከጥርጣሬ ይልቅ በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
ይህም ኢትዮጵያን የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ከበባ እንድትሰብር ከማድረጉም ባለፈ፣ በመሠረተ ልማትና በታዳሽ ኃይል አቅርቦት አማካኝነት የአገራችንን ቀጣናዊ ተፅዕኖ በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል፡፡
ባሳለፍናቸው የለውጥ ዓመታት በርካታና ውስብስብ ፈተናዎች ተጋፍጠናል፡፡ ግጭቶችና ከፍተኛ የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን አስተናግደናል፡፡ ሆኖም ግን በተደረገው የሕዝባችን ትብብር፣ በአመራር ቁርጠኝነትና ጥበብ የተጋረጡብንን ፈተናዎች ተቋቁምን መሻገር ችለናል።
በተለይም በዚህ ዓመት ኢትዮጵያን ሊያሻግሩ የሚችሉ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጅቶችን በብቃት በመምራት በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት ማጠናቀቅ ተችሏል። የጋራ አሻራችንና የአንድነታችን ተምሳሌት የሆነው ታላቁ ሕዳሴ ግድባችን አጠናቀን ለፍሬ አብቅተናል።
ድሬዳዋ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በከፍተኛ የብልፅግና ግስጋሴ ላይ ትገኛለች።
ከተማዋ በአሁን ሰዓት በዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን ወክላ እንዲሁም አፍሪካን ወክላ ትልልቅ መድረኮች ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች። ይህም ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የሚሰጡ አቅጣጫዎች በአስተዳደሩ በውጤታማነት እንዲተገበሩ ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በከፍተኛ በቁርጠኝነት በመስራታቸው የተገኘ ዕምርታ ነው።
የከተማዋ የኖረ የአብሮነት የፍቅርና የሰላም እንዲሁም የእንግዳ ተቀባይነት እሴት በለውጡ አመታት በከፍተኛ ሁኔታ አድጎ ከተማዋን በርካታ አንባሳደሮች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ጎብኝተዋታል።
ይህም ድሬዳዋ በአለም አቀፍ መድረኮች እንድትተዋወቅ በር ከፍቷል። ድሬዳዋ ከአውሮፖ፣ ከአፍሪካና ከኤዢያ ከተሞች ጋር እህትማማች ከተማ ስትሆን ከ 15 በላይ ከሚሆኑ ከተሞች ጋር ሲስተር ሲቲ ተፈራርማ ወደስራ ገብታለች።
የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆችን በየአመቱ የሚያሰባስበው “የናፍቆት ድሬ ሳምንት” የድሬዳዋን ልማትና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፆ አለው።
በዓሉ በመላው አለም የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆችን ከማሰባሰቡ ባሻገር የህዝቡን ማህበራዊ ችግሮች በማቃለሉ ረገድ እንዲሁም ዲያስፖራው ማህበረሰብ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ ሀገሩን እንዲጠቅም መደላደልን ፈጥራል።
በአጠቃላይ ባለፉት ስምንት ዓመታት እንደሀገር የተመዘገቡት ስልታዊ የዲፕሎማሲ ድሎች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ከፍታ አሸጋግረውታል። ዛሬ ሀገራችን በውጭ ግንኙነቷ የምትታወቀው ድጋፍ በመጠየቅ ሳይሆን የቀጣናዊ አጀንዳዎች ምንጭና የመፍትሔ አካል በመሆን ነው። ይህ አዲስ ገጽታችንና እየተገነባ ያለው ብሔራዊ ኩራት ለሚገጥሙን ማናቸውም ጫናዎች እንዳንበረከክ አቅምና የልማት ጉልበት ሆኖናል።


