በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን መድኃኒት ሙሉ በሙሉ በራሷ አቅም እንደምታመርት ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባውን ዘመናዊ የምርምር ማዕከል መርቀው በከፈቱበት ወቅት ኢትዮጵያ በመድኃኒት ምርት ራስን ለመቻል የሄደችበትን ርቀት አብራርተዋል።
በአንድ ሀገር ውስጥ ችግር እና ተግዳሮቶች ሲፈጠሩ ከመሸበር ይልቅ ችግሩን እንደ ዕድል መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ያጋጠመውን ችግር አስታውሰዋል።
በሰዓቱ ወረርሽኙ ሲከሰት ኢትዮጵያ የራሷን የመድኃኒት አቅርቦት ለመሸፈን የምታመርተው የመድኃኒት መጠን 8 በመቶ ብቻ መሆኑን አንሥተው በሰዓቱ የነበረው ችግር ኢትዮጵያ በመድኃኒት አቅርቦት ራሷን መቻል እንዳለበት ያመላከተ ጊዜ ነበር ብለዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተሰሩ ሰፊ ሥራዎች ኢትዮጵያ አሁን ላይ 44 በመቶ ለራስ ፍጆታ የሚሆነውን መድኃኒት ማምረት ችላለች በቀጣይ ሳምንታት በሚመረቁ ፋብሪካዎች አማካኝነት ቁጥሩ እስከ 55 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
“አንድ ሀገር ምግብ፣ ልብስ እና መድኃኒት በራሱ ማምረት ካልቻለ ሉዓላዊነቱ ጥያቄ የሚያስነሣ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ለራሷ የሚያስፈልጋትን መድኃኒት ታመርታለች በምግብ እና በልብስ ያመጣችውን ስኬት በመድኃኒት ላይም ታሳካዋለች ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው የምርምር ማዕከል መድኃኒት ለማምረት የሚደረገውን ምርምር የሚያሳልጥ ነው።
ላብራቶሪው ከዚህ ቀደም ምርመራዎችን ወደ ውጪ የመላክ ሂደት የሚያስቀር ነው ብለዋል።


