ኢትዮጵያ በመድኃኒትና በክትባት ምርት ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ግዙፍ የምርምር ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማዕከሉን በመረቁበት ወቅት፥ ከዚህ ቀደም ይህን መሰል መሰረተ ልማት ባለመኖሩ “ኢትዮጵያ መድኃኒትና ክትባት ማምረት አትችልም” በሚል የምናቀርበውን የአጋርነት ጥያቄ ብዙዎች ሳይቀበሉት ቀርተዋል ብለዋል።
የዚህ ዘመናዊ የምርምር ማዕከል መገንባት ያንን ታሪክ የቀየረ ታላቅ ድል ስለመሆኑም ገልጸዋል።
ማዕከሉ የመድኃኒት ጥራት ማረጋገጫ፣ ለዓለም አቀፍ አምራቾች አስፈላጊ የሆኑ ሳይንሳዊ መረጃዎች እንዲሁም 40 የላቁ ላቦራቶሪዎችን ያካተተው ማዕከሉ፣ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ብቃት የሚያረጋግጥ አገልግሎት ባለቤት የሚያደርገንም ነው ብለዋል።
ከዓመታት በፊት የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ እንዲህ ያሉ ማዕከላት ለሀገራችን ምን ያህል አስፈላጊ መሆናቸውን እንድንገነዘብ ያደረገ ስመሆኑ ጠቅሰው፤ ተቋሙ ምርምርን ወደ ተግባራዊ መፍትሔ በመቀየር ረገድ እንደ ማገር ሆኖ እንደሚያገለግልም አክለዋል።
ኢትዮጵያ በመድኃኒት ዘርፍ የጀመረችው ይህ የብቃት ጉዞ ጤናማና በራሷ የምትተማመን ሀገር ለመገንባት የተጣለ ትልቅ መሠረት ነው።


