‎”ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን!” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የከተማችንን እድሳት ለማፋጠን እና የዜጎቻችንን ክብር ለመመለስ የገባነውን ቃል አንዱ ማረጋገጫ የሆነውን የአዲስ ስፖርት ፓርክን በይፋ መርቀን ከፍተናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር መተግበሪያ ባጋሩት መልዕክት።

በ5.7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ፕሮጀክት፤ በኦሎምፒክ መድረክ ለሀገራችን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ 15 አትሌቶችን የሚዘክሩ የክብር ሐውልቶችን በፓርኩ መሃል በማቆም፣ የጀግኖቻችን ታሪክ ለተተኪ ትውልድ ስፖርተኞች ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል ብለዋል።

የኦሎምፒክ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስና የሜዳ ቴኒስ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የ800 ሜትር የሩጫ ትራክን ጨምሮ፤ እያንዳንዱ የዚህ ማዕከል ክፍል የዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ተደርጎ ተገንብቷል ነው ያሉት።

‎የእውነተኛ ልማት ማዕከል ማህበረሰቡ ላይ መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ይህ ፕሮጀክት ከላቀ የስፖርት አገልግሎት ባለፈ፣ በልማቱ ምክንያት ለተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅም የሚሆኑ 105 አዳዲስ የንግድ ሱቆችን እንዲሁም 3 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ፕላዛ መያዙን ጠቅሰዋል።

በአንዴ 300 መኪናዎችን የሚይዝ ባለ ሁለት ወለል የምድር ቤት መኪና ማቆሚያ ያለውና ከወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር የተሳሰረው ይህ ፓርክ፤ ንፁህና ዘመናዊት ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የጀመርነው ቁርጠኝነት ጉልህ ማሳያ ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *