7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ስርዓት ለማፅናትና ሀገራዊ የመግባባት ዴሞክራሲን ለመትከል መሠረት የሚጣልበት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ እሙን ነዉ።
በዛሬው እለት የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የጋዜጠኞች ቡድን ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ምርጫ ካርድ የወሰዱ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ህብረተሰብ የመራጭነት ካርድን በመውሰድ የዜግነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ በተሰጠው ዲሞክራሲያዊ መደላደል ተጠቅሞ ይበጀኛል ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ የመምረጥ መብቱ በእጁ መሆኑን አውቆ ለተፈጻሚነቱ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባም ነዉ የገለጹት።
አስተያየት ሰጪዎቹ በመቀጠልም መላው ህብረተሰብ የመራጭነት ካርዱን በተቀመጠው ጊዜ ገደብ በመውሰድ እና በሁሉም ወረዳዎቻቸው ውስጥ በሚገኘው የምርጫ ጣቢያዎችንና በኢንተርኔት ደግሞ በቀላሉ በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው በመጠቀም በየትኛውም ሥፍራ ላይ ሆነው በማንኛውም ሰዓት የምርጫ ካርዶቻቸውን በመውሰድ፣ የመራጭነት መብታቸውን መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል።
በመስተንግዶ ሞያ የተሰማራችው ያነጋገርናት ወጣት ኤልሳቤት በንቲ ስትገልጽም የመራጭነት ካርዱን በተቀመጠው ጊዜ ገደብ መውሰዷን እና በየትኛውም የሙያ ዘርፍ የሚገኝ ዜጋ ካርድ በመውሰድ የመራጭነት መብቱን መጠቀም እንደሚገባ ገልጻለች።
በሊስትሮ ሞያ የተሰማራው ወጣት ታደለ ገብሬ እንደተናገረው በስራ ጫና ምክኒያት ሳይመዘገብ መዘግየቱን ገልጾ በምርጫዬ ሞባይል መተግበሪያ በቀላሉ ባለበት ሆኖ ምርጫ ካርድ መውሰዱንም ተናግሯል።
በዘንድሮ በ7ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የምርጫ ካርድ ለመውሰድ በዲጂታል አማራጭ ባሉበት ሆነው በሞባይል መተግበሪያ እና በአካል በመገኘት በአቅራቢያዎ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ በመሄድ ተመዝግበው የምርጫ ካርድ ለመውሰድም አማራጮች መኖሩ ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናልም ነዉ ያሉት።
በመሆኑም በተራዘመው ተጨማሪ ጊዜ ተጠቅሞ የመራጮች ምዝገባ በማካሄድ፤ በሁሉም አካባቢዎች ሕብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ የመራጭነት ካርድ እንዲወስድም ሲሉም ነው ጥሪ ያቀረቡት።


