“የመራጮች ምዝገባ ካርድ በመውሰድ በሀገር ጉዳይ መወሰን እንዲሁም የዜግነት ግዴታን መወጣት ይገባል”:- የድሬዳዋ ነዋሪዎች

የመራጮች ምዝገባ ካርድ በመውሰድ በሀገር ጉዳይ መወሰን እንዲሁም የዜግነት ግዴታን መወጣት ይገባል ሲሉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በድሬዳዋ አስተዳደር ‎የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ ታዲያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደትን እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ያራዘመ ሲሆን ይህንን እድል በመጠቀም በተሰጠው ጊዜ “እኛ ነገ የሚመራንን መንግስት ለመምረጥ የሚያስችለንን የምርጫ ካርድ ወስደናል መላው የድሬዳዋ ነዋሪም ካርዱን በጊዜ እንዲወስድ ጥሪ እናቀርባለን” ሲሉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ነዋሪዎቹ ጠንካራ መንግስት ለመመሰረት የሚያስችለው በህዝብ ድምፅ መሆኑን በመጠቆም ድምፃችንን ለመስጠት የምርጫ ካርዳችንን ይዘን መገኘት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ በሁለት መንገድ መመዝገብ መቻሉ ሂደቱን ቀልጣፋ ማድረጉን ነዋሪዎቹ ጠቁመው፤ ያለምንም እንግልት ባሉበት ቦታ ሆነው “ምርጫዬ” የተሰኘ መተግበሪያን ከአፕ-ስቶር ወይም ከፕለይ-ስቶር አውርደው በመጠቀም የመራጭነት ካርድ መውሰድ መቻላቸውን እንዲሁም በየወረዳዎቹ በሚገኘው የምርጫ ጣቢያዎች ድረስ በመሄድም በአካል መመዝገብ መቻላቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።

ነዋሪዎቹ አያይዘውም ዓለም በቴክኖሎጂ እየዘመነ ባለበት ወቅት ሀገራዊ አሰራሮችን ለማዘመን የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፤የዘንድሮው ምዝገባ በምርጫ ጣቢያዎች ከሚካሄደው በተጨማሪ በኦንላይን መከናወኑ ጊዜን ከመቆጠብ ባለፈ የምዝገባ ወረፋን እንዳስቀረላቸው አብራርተዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም ሀገራዊው ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ የመራጭነት ካርዳቸውን በመውሰድና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ለሀገር ይበጃል ያሉትን በመምረጥ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ካነጋገርናቸው ህብረተሰቦች መካከል በተለይም ሴት አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው በምርጫ ወቅት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረው፤ ይህ ሀገራዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎኣቸውን፣ ሁለንተናዊ ጥቅሞቻቸውን እና ፍትኃዊነትን ይበልጥ የሚያስጠብቁበት ታላቅ ሂደት መሆኑን ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *