በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ አስተዳደር በሴቶች አስተባባሪነት የተዘጋጀ የብልፅግና ፓርቲ የአደባባይ የምርጫ ቅስቀሳ በድምቀት ተካሂዷል።
በዚህም በቅስቀሳው ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ፓርቲው ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ኑሮ ለማሻሻል የወሰዳቸው እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም ብልፅግና ፓርቲ የሴቶችን የኑሮ ጫና የሚቀንሱ የልማት ሥራዎችን በተግባር በማሳየቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አመላክተዋል።
በአስተዳደሩ የተገነቡ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትና መሰረተ ልማቶች የሴቶችን የዕለት ተዕለት ጫና በመቀነስ ረገድ ትልቅ ለውጥ ማምጣታቸውን ተሳታፊዎቹ ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም ለተደራራቢ የቤት ውስጥ ሥራዎች ይባክን የነበረው ጊዜ አሁን ለምርታማ ተግባራት፣ ለትምህርትና ለሌሎች ማህበራዊ ተሳትፎዎች እንዲውል መደረጉ ብልፅግና ፓርቲ ለሴቶች ያለውን አጋርነት በተግባር ያሳየበት እንደሆነ ገልፀዋል።
በወጣቶችና በሴቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በብድር አቅርቦት እንዲሁም በገበያ ትስስር ዙሪያ የታዩ ማሻሻያዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎች፤ ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ደረጃ እንዲመጡ የተደረገው ጥረትም በራሳቸው እንዲተማመኑ ማድረጉን አመልክተዋል።
በመጨረሻም አስተያየት ሰጪዎቹ የስንዴ ነዶን መምረጥ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አጠናክሮ ማስቀጠል መሆኑን ገልፀው፤ በአጠቃላይ የብልፅግና ጉዞ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የተሻለ ነገን ለመገንባት የስንዴ ነዶን መምረጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።


