የመረጃ አያያዝ ክፍተትም ለህገ-ወጥነት በር ከፍቷል፡፡
አቶ እውነቱ ወርቅነህ
የድሬዳዋ አስተዳደር ቤቶች ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ የሆነው የድሬዳዋ አስተዳደር ቤቶች ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የስድስት ወራት የስራ አፈጻፀሙን ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
በአፈፃፀሙም በርካታ ያልተከፈሉ ውዝፍ እዳዎችን የማስከፈል፣ በህገ ወጥነት የተያዙ ቤቶችን የማስመለስ፣ ከእገዳ በፊት የኮርፖሬሽኑን መመሪያ ለደንበኞች ቀድሞ የማስተዋወቅ፣ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ በገቢ እራሱን እንዲችል እንዲሁም ህገ ወጥነትን ለማስቀረት የመረጃ ቋት አያያዝን በኮምፒዩተር ቋት በመጠቀም ለማዘመን ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ ስራ አስኪያጅ አቶ እውነቱ ወርቅነህ አስታውቀዋል፡፡
ደንበኞች በተለይም የመንግስት ኃላፊነት ያላቸው አመራሮች ከኃላፊነታቸው ሲነሱ ይኖሩባቸው የነበሩ የኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤቶችን ለተተኪው አመራር በህጋዊ መልኩ ለማስተላለፍ ያለመፈለግ ችግርና መስሪያ ቤቱ ምንም አይነት መረጃ ሳይኖረው ለሌሎች ሰዎች ተላልፎ የመገኘት ሂደት በተጨባጭ መረጃን እያዛባና ቤቶችን በፍትሃዊነት ለማስተላለፍ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
አቶ እውነቱ የቤቶችን ካርታ ሰርተፍኬት ወደ ዳታ ቤዝ በማስገባት እንዲሁም ካርታ ካልነበራቸው 1 ሺ 109 ቤቶች ውስጥ 4 መቶ 18 የሚሆኑትን ካርታ በመስጠት ቀሪዎቹን ለማጠናቀቅ ከአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ህገ ወጥ ደላሎች ቤቶችን በማሻሻጥ በአብዛኛው አሁን ላይ ያሉት የቤቶቹ ደንበኞች በኮርፖሬሽኑ የሚታወቁ ሳይሆኑ ሶስተኛ ወገን መሆናቸውን ብዙ ጥቆማዎች እንዳሉና ኮርፖሬሽኑ በዚህ ዙሪያ ምን እየሰራ ነው ሲሉ ጋዜጠኞች ላነሱላቸው ጥያቄ አቶ እውነቱ ሲመልሱ ደላሎች ብቻ ሳይሆኑ የኪራይ ሰብሳቢነት አባዜ ያለባቸው የውስጥ ሠራተኞችም ጭምር በዚህ ተግባር ውስጥ እንደሚሳተፉ በተጨባጭ መረጃዎች እንዳሉ ገልፀው፤ ይህንንም በውስጥ አሰራር የማስተካከል ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆኑና አሠራሮችን በማዘመን እንዲህ አይነት ድርጊቶች መደረግ እንዳይችሉ የማስቻል ስራ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀው፤ ከዚህ ድርጊታቸው የማይቆጠቡትን ግን በህግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚያደርጓቸውም አሳስበዋል፡፡
ከአስተዳደሩ በተገኘው 4.4 ሄክታር መሬት ላይም በቀጣይ አመታት የንግድ ቤቶችን ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት አሰርተው ማጠናቀቃቸውንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡


