የምስራቅ ሀረርጌን ሠላም ለማስመለስ የወጣቶች ሚና የጎላ ነው ተባለ ከሁሉም ቤተ እምነት የተውጣጡ ወጣቶች ‹‹የክርስቲያንና ሙስሊም ግንኙነት ለሠላም- በወጣቶች›› በሚል መርህ የተዘጋጀ የሰላም ውይይት መድረክ ከድሬዳዋና ሐረር ከተማ ከተወጣጡ ወጣቶችና የሀይማኖት መሪዎች ጋር በድሬዳዋ ተካሂዷል፡፡

    የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኖርዌይ ቤተክርስቲያን የእርዳታ ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ ላይ ተሣታፊ የሆኑ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት ወጣቶች በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ለሠላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡
    በመድረኩ መክፈቻ ላይ ያለን ሀገር አንድ ነው፡፡ አንድ አይናማ በአፈር አይጫወትም ያሉት ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ የኢትዮጲያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሀፊ አንድ ሀገር ያለንና ሌላ ማምለጫ የሌለን ህዝቦች ሆነን ሳለን በዚህች ሁሉም ተዋዶ ለሺዎች አመታት በኖረባት ሀገር እጣ ፈንታ ላይ ተነጋግረን ችግሮቻችንን መፍታት ካልቻልን ኪሣራ ውስጥ ነን ብለዋል፡፡
    የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች እንደመሆናቸው ወጣቱን ያካተተና ያሣተፈ መርሀ ግብር በተለይም በሃይማኖት ውስጥ አሁን ያለውን ሁኔታ መገንዘብ እንደሚቻለው አንድ ጊዜ የብሔር ሽፋንን ይዞ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ አላማ ያለው፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሀይማኖት ተቋማትን አላማ ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፡፡ ይህንን በሁሉም ቤተ እምነቶች በተለይም በክርስትና እና በእስልምና ሀይማኖቶች ውስጥ በመመሪያዎቻቸው ወይም በመፅሐፍቶቻቸው ውስጥ ለግጭት የሚዳርግ ምንም ቅድመ ሁኔታ በሌለበት የግለሰቦች ፍላጎት ሲከሰቱ እየተመለከቱ መሆኑን የጠቆሙት በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ተሣታፊ የነበሩ የሀይማኖት አባቶች ናቸው፡፡
    ግጭቶችን በውይይት ለመፍታትም ብሎ አርቆ ማሰብ እንደሚገባም የውይይቱ ተሣታፊዎች ተማምነውበታል፡፡ ለሀገር ኪሣራ ነገ ተጠያቂ የዛሬው ትውልድ መሆኑንም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
    መጋቢ አሌፍ ቢንያም ከምሥራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመጣ ሲሆን ምስራቅ ሀረርጌ በስፋት የእስልምናና የክርስትና ሀይማኖት እምነት ተከታዮች የሚኖርበት እንደመሆኑ ማህበረሰቡ ቀድሞ የነበረውን የአብሮነት እሴቶች ይዘው እንዲቀጥሉ ለማስቻል የዚህ አይነቱ መድረክ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
    ግንዛቤ ከማጣት የተነሣ ብዙ ችግሮች ሲከሠቱ ማስተዋላቸውን የተናገሩት መጋቢው ነገር ግን ለወጣቶች በየጊዜው ስለ መልካም ስብዕና ግንዛቤ ቢሰጥ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የትኛውም እምነት የሚሰብከው ሰላምን በመሆኑ ወጣቶች መከተል ያለባቸው የቤተ እምነታቸውን መልዕክት እንጂ የሌሎችን መሆን እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡
    ከድሬዳዋ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ተወክላ የመጣችው ተሣታፊ ወ/ሪት ምስራቅ ሙሉጌታ ወንጌላችን የሰላም ወንጌል ስለሆነ ሁሉም ህብረተሰብ ይህንን እንደ ስብከት ሳይሆን ወደ ራሱ ወስዶ በመፀለይ የሀገሪቱ ሠላም እንዲመለስ ከመንግስት በበለጠ ኃላፊነት አለበት ስትል አስተያየቷን ሠጥታለች፡፡