መድረኩ የተካሄደው ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ለተውጣጡ እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ነው፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በኮቪድ-19 ምክኒያት ወረርሽኙን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በአዋጁ መሰረት ስንመራ የነበረ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ኮቪድ-19ን ከመከላከል አንፃር ዝንጉነት እንዳይፈጠር በጤና ጥበቃ ሚ/ር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን መመሪያውን ማዘጋጀታቸውን አውስተዋል፡፡
ኃላፊዋ ጨምረውም መመሪያው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ተቀምጠው የነበሩ እንደ ሰርግ፣ የአስክሬን አያያዝ፣ የቀብር አፈፃፀም፣ ሃዘን፣ ስብሰባዎችና የተለያዩ ማህበራዊ ክንውኖቻችን ምንም እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ ቢሆንም በምን መልኩ ሊተገበሩ ይገባል ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥና ግዴታዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የተቀመጠው መመሪያ እያንዳንዱን ዜጋ ተጠያቂና ጠያቂ የሚያደርግ ሲሆን በትራንስፖርት ላይ፣ በግብይት ቦታዎች እና ማህበራዊ አገልግሎቶች በሚሰጡባቸው ስፍራዎች ወዘተ የሚስተዋሉ የመመሪያ ጥሰቶችን ሁሉም በኃላፊነት እንዲተገብር እና ባለመተግበሩም ጠያቂ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ መመሪያውን በተመለከተ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎችም የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡
በተለይ በትራንስፖርት አጠቃቀም ወቅት ማስክ ማድረግና የሚወጡ መመሪያዎችን ከማስፈፀም አኳያ ያሉ ክፍተቶች በምን መልኩ ይፈቱ የሚሉ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡
ጥያቄዎቹም ይሁኑ አስተያየቶቹ ገንቢ መሆኑን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ለምለም መመሪያውን ለሁሉም የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ሚዲያውን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡ ሆኖም ግን ህብረተሰቡ እራሱንና ሌሎችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለማዳን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመመሪያው የተደነገጉ ክልከላዎችና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ተቋማት አግባብነት ባለው የወንጀል ህግ መሰረት ተጠያቂ የሚሆኑ ሲሆን መመሪያው ከ መስከረም 25/2013 ዓ/ም ጀምሮ የጸና መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ምንጭ ፡ የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ


