አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጣር የወጣውን መመሪያ ቁጥር 30/2013 መጣስ እስከ ሁለት አመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ማሳሰቢያን መሠረት በማድረግ የወረርሽኙን መስፋፋት ለመቀነስ ያስችል ዘንድ የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ እና መመሪያዎችን በማውጣት ስትተገብር መቆየቷን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውሷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላም በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጣር የወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013 በተለያዩ አካላት ማለትም በግለሰቦች፣ በመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እና በድርጅቶች ላይ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን መጣሉንም ነው ያስታወሰው።
ክልከላዎቹን መተላለፍ እና ግዴታዎቹን አለመወጣት አግባብ ባለው የወንጀል ሕግ እንደሚያስቀጣ በመመሪያው ተደንግጎ ይገኛልም ብሏል።
ከዚህ አንጻር በመመሪያው የተካተቱ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ መሠረት የሚቀጣ መሆኑን በመመሪያው አንቀፅ 30 ላይ ማስቀመጡንም ጠቅሷል፡፡
ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የወንጀል ሕግ በ1996 ዓ.ም የወጣው የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 522 መሆኑንም አመላክቷል።
ህብረተሰቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር ራሱን እና ሌሎችን ከወረርሽኙ እና ከሚያስከትለው ጉዳት እንዲጠብቅና በመመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎች እና ግዴታዎችን መጣስ ከሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት እንዲጠበቅም ጥሪውን አቅርቧል፡፡


