የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን በመከላከል የ2013 የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማስጀመር ውይይት አካሄደ፡፡

    በዩኒቨርሲቲው ውስጥም ተማሪዎችን በዘር፣ በሀይማኖትና በብሔር የሚከፋፍሉ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራኞች ላይ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ እንደማይታገስ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ተቋማት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አለሙ ስሜ ገልፀዋል፡፡

    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የ 2013 የትምህርት ዘመንን ለማስጀመር ይረዳ ዘንድ የተለያዩ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎችን በማከናዎን ላይ የሚገኝ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ያሉትን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችንም ከዚህ ቀደም የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባላት ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም ከወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ ጋር ተያይዞ ትምህርት ለማስጀመር ይቻል ዘንድ እያከናወናቸው ያሉትን ስራዎችና ከዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባላት ጋር ትውውቅን በማድረግ በቀጣይ አብረው በሚሰሩባቸው ስራዎች ዙሪያ እንዲሁም ሰላማዊ በሆነ አግባብ የመማር ማስተማሩ ይካሄድ ዘንድ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳትና የቦርድ አባላት በተገኙበት ከዩኒቨርሲቲው ሰራተኞችና መምህራን ጋር ውይይት የተካሄደ ሲሆን በውይይቱ ላይም በተለይም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው በሚገቡበት ጊዜ ስለ ኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ በቂ የሆነ ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ የሳኒታይዘር የአፍና አፍጫ መሸፈኛ ማስኮች እንዲሁም የመጠጥ ውሀ የመማሪያ ክፍሎችና መገልገያ እቃዎች እንዲዘጋጁና ከፀጥታ ስራዎች አንፃርም በትኩረት መሰራት እንዳለበት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞች ጠይቀዋል፡፡

    ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ ጋር ተያይዞ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎችን ከበሽታው የመጠበቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው  የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ተቋማት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አለሙ ስሜ ገልፀው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተማሪዎችን በዘር፣ በሀይማኖትና በብሄር የሚከፋፍሉ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራኞች ላይ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ እንደማይታገስም ዶ/ር አለሙ ስሜ ተናግረዋል፡፡

    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከመሰረተ ልማት ስራዎች ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በቀጣይ እንደሚሰራ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም ተናግረው በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማርን ከማስጠበቅ አኳያ የሁሉም ባለድርሻ አካላትና ነዋሪዎች ሀላፊነት እንደመሆኑ መጠን በጋራ መስራት እንደሚገባም  ዶክተር ኡባህ አደም ተናግረዋል ፡፡

    ይህ በእንዲህ እንዳለም ሰላማዊ የመማር ማስተማር በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እንዲሰፍንና ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ለማረም እንዲያግዝ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አቀፍ አማካሪ ምክር ቤት  ተመስርቷል፡፡ የተመሰረተው ምክር ቤትም በድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና በዩኒቨርሲቲ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አህመድ መሀመድ ሰብሳቢነትና የፍትህ የፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሙሳ ጣሃ በምክትል ሰብሳቢነት ይመሩታል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ታዋቂ ግለሰቦችና የኃይማኖት አባቶች፣ ኡጋዞች፣ አበገዳዎች ፣ሱልጣኖች፣ ወጣቶች በምክር ቤቱ አባልነት ተካተውበታል ፡፡