ህብረተሰቡ ሰላሙን በማስጠበቅ እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህሉን እንዲያጠናክር ጥሪ ቀረበ።

    የድሬደዋ አስተዳደር በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሀይማኖት አባቶች ጋር ወይይት አድርገዋል። በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሀር ድሬዳዋ ያሳለፍናቸው ወራት በህብረተሰቡና በፀጥታ አካላት ትብብር ብዙ ዋጋ በተከፈለበት መስዋዓትነት ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለሷን በመጠቆም ይህንን ሰላም ሊያደፈርሱ የሚፈልጉ ቀን ከሌት የማይተኙ በሰው ህይወት ቁማር የሚጫወቱ አረመኔ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲጠፉ እና የህግ የበላይት እንዲረጋገጥ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
    ምክትል ከንቲባው አክለውም ህብረተሰቡ ነቅቶ አከባቢውን፣መንደሩንና ጎረቤቱ በመጠበቅ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮቹን አስመልክቶ የመንግስት መረጃ ተቋማትን እንዲከታተሉ ጠቁመዋል፡፡ ቤተ-እምነቶች እንደ ወትሮ ሁሉ የእምነት ተከታዮቻቸውን ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ለሰላማቸው ዘብ እንዲቆሙ ተከታታይነት ያላቸው ትምህርቶችና ግንዛቤ ለህብረተሰቡ ማድረሰ መቻል እንዳለባቸው ምክትል ከንቲባው አስገንዝበዋል።
    የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ መንግስት ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ የሚያደርገውን ሆደ ሰፊነትና ትዕግስት የሚያበረታታ ቢሆንም ሀገርና ህዝብ ላይ ጉዳት የሚያደረሱ ሀይሎችን ከህዝብ ጋር በመሆን የሀገራችንን ህልውና ማስቀጠል መቻል አለበት ብለዋል። የእምነት አባቶቹም መንግስት ለህብረተሰቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መረጃዎችን በፍጥነት በሚዲያ በኩል እንዲያደርሱ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ የእምነት አባቶች ከዚህም ጋር በማያያዝ ህብረተሰቡ ከመንግስት የሚሰጡትን መረጃ ብቻ እንዲከታተሉና በተለይም ሀሰተኛ ወሬዎችን እንዲጠነቀቁ አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም የእምነት አባቶቹ በሀገራችን እና ህዝቧን ከጠላት ፈጣሪ እንዲጠብቀን ፀሎት በማድረግ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡