የመማር ማስተማር ስራዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥሉ የመምህራን የሙያ ብቃትና በተለይም ብቁ ዜጋ ከማፍራት ጎን ለጎን የሀገራችን የብልፅግና ጉዞ መምህራን የላቀ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ከንቲባ ክቡር አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ አንደገለፁት ዛሬ በዓለም ላይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ሀገሮች ለስኬታቸው ዋናው ምክንያት ለትምህርት ትኩረት በመስጠታቸው ሲሆን በዚህ ረገድ መምህራን ሙያቸውን በመውደድና በማክበር ብቁ ዜጋ የማፍራት ተልኳቸውን የመወጣት ሀገራዊና ሙያዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ክቡር ከንቲባው አክለውም አስተዳደሩ አቅም በፈቀደው መጠን መምህራንን ሲደግፍ መቆየቱን ገልጸው በቀጣይም ለመምህራን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡ መምህራን በተለይም ኮቪድ 19 እየተከላከልን የትምህርት መህበረሰብ ጤንነት ለአደጋ በማያጋልጥ ሁኔታ የሚከናወነው የመማር ማስተማር ስራ ሊፈጥር የሚችለውን የስራ ጫና ጊዜአችሁን በመሰዋት ትውልድን በአግባቡ ለመቅረፅ የተጣለባችሁን ሀላፊነት በትጋትና ፅናት እንድትወጡ ሲል ከአደራ ጭምር አሳሰበዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ በበኩላቸው ቢሮው ባለፉት አመታት የመምህራንን ጥቅም ለማስከበር ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱንና በዚህም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል ። ለረጅም አመታታት የመምህራን ጥያቄ ሆኖ የቆየው የመኖሪያ ቤት ጥያቄ አስተዳደሩ በሰጠው 12 ሄክታር መልስ ማግኘቱንም አብራርተዋል ። በዕለቱ የዝግጅቱ ተካፋይ የነበሩት መምህራን በተለይም መንግስት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለመጀመሪያ የመምህራንን ቀን በዚህ አይነት ደማቅ ዝግጅት መክበሩ ለመምህራንና የትምህርት የሚሰጠው ትኩረት ከፍ ያለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“የመምህርነት ሙያ ከየት ወዴት ?” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሁፍም በቢሮው የመምህራን ልማት ከፍተኛ ባለሙያ በአቶ አረፋት ሙሳ ቀርቦ መምህራን የተወያዩ ሲሆን በመምህርነት ሙያ ለረጅም አመታት አገልግለው ጡረታ ለወጡ 34 አንጋፋ መምህራኖች እንዲሁም በስራ ላይ ያሉ እና በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ 32 ምስጉን መምህራን የእውቅና ሰርትፊኬት እና የገንዘብ ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዶች እጅ ተቀብለዋል ።


