በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል ተባለ::

    የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት÷ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለሃብቶች እና ባለድርሻ አካላት የትስስር ፎረም ለመመስረት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።
    በመድረኩ የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሐር በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ወሳኝ ከሚባሉት በተለይ ከሰው ሀይል÷ የማቴሪያል÷ከማምረቻና ከመሸጫ ቦታ ምችችትን ጨምሮ ከመብራትና ከብድር አቅርቦት እረገድ የተለያዩ ችግሮች እንደሚስተዋሉ አስረድተዋል።
    ችግሩ በተለይም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት መካከል ትስስራዊ አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ጨምረው ገልጸዋል። የትስስር ፎረም መመስረቱ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስቀረት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ያስችላል ነው ያሉት አቶ ከድር ጁሐር።
    በተመሳሳይ የድሬደዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ም/ኃላፊ ና የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ዳይሬተር አቶ አብዲ ሙክታር በዘርፉ ያሉ ተዋናዮች የተጠናከረ ቅንጅታዊ አሰራር ባለመኖሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዳይመዘገብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
    በቀጣይ ቅንጅታዊ የአሰራር ቅብብሎሽን በማሳለጥ ዘርፉ እንደ አስተዳደርም ሆነ እንደ አገር ለኢኮኖሚው የሚኖረውን ሚና የላቀ እንዲሆን እንደሚችል ም/ቢሮ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።
    በመድረኩ በርካታ ሃሳብና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በቀጣይ ፎረሙ በየሶስት ወር የግንኙነት መድረክ እንደሚኖረው ለማወቅ ተችሏል።