እኩልነትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የዘንድሮ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ችቦ ድሬደዋ ገባ፡፡

    ችቦው በሶማሌ ክልል ርዕስ ከተማ የሆነችው ጅግጅጋ ከተማ ተለኩሶ በሀረሪ ብሄራዊ ክልላዊ ርዕስ ከተማ ሀረር ደርሶ በዛሬው እለት የሀረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ አዲስዓለም በዛብህ እና የክልሉ ሉዕካን ቡድን ለድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ለወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ አስረክበዋል፡፡
    የችቦ መቀበል ስነ-ስርዓቱ ላይ የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ፣ ም/ከንቲባና ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቬስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጀውሃር ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየስ፣ የአስተዳደሩ ካቢኔ አባላት፣ የሀገረ ሽማግሌ፣ የሀይማኖት አባቶች እና ጥሪ እየተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
    በመድረኩ ላይ የእንኳን በደህና ወደ በረሀዋ ንግስት ድሬደዋ መጣቹ መልዕክት ያስተላለፉት የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ እንደተናገሩት ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀን የሚከበረው የመጀመሪያው ስርዓት የህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያሳይ ችቦ ስነ-ስርዓት በህዳር 29 የብሄር ብሄረሰቦችና የህገ-መንግስቱ ቀን በሆኑ ሀገራችን የሚያስፈልጋትን የለውጥ መንገድ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝቦች ከነበረባቸው ጭቆናና በሰፊው ህዝብ የተጀመረው የለውጥ ፋላጎት ወደ ፓርቲያችን መሪነት ይሄው የለውጡ ፍሬ መቅመስ ተችሏል ብለዋል፡፡
    የሀረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ አዲስዓለም በዛብህ የችቦ መረካከቢያ ስነ-ስርዓቱ ላይ በተለይም ይህንን ችቦ በ04/03/2013 ዓ/ም ከሶማሌ ክልል ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ እንክብካቤ፣ የጽዳት ዘመቻና የተለያዩ የበጎ ሥራዎች በተለይም በደም እጦት የሚሰቃዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የደም ልገሳ መርሀ-ግብር የተካሄዱ ተግባራት ናቸው ብለዋል፡፡
    የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ በበኩላቸው የዘንድሮ የ15ኛ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል የህዝቦች ሁለንትናዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ከማረጋገጥ አንፃር የሀገራዊ ለውጥ ውስጥ በምንገኝበት እስከ አሁን በነበረበት ህገ-መንግስታዊና ፌደራላዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት የነበሩበት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያረመን በምንገኝበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ከሌላው ጊዜ የተለየ ያረገዋል ብለዋል፡፡
    በመድረኩ የችቦ መለኮስ ስነ-ስርዓት እና በተለይም አስተዳደሩን በመወከል ችቦውን በከተማው ጎዳና የሚያዞሩ እና ለተረካቢው አፋር ክልል የሚያስረክቡ ሴት ሞዴሎች ተመርጠዋል፡፡ በዛሬው እለትም በአስተዳደሩ ጎዳና ላይ በማርሽ ባንድ ታጅቦ እንደሚዞዞር ከመድረክ ተጠቁሟል።
    በቀጣይም ችቦው በአስተዳደሩ በቆይታው ጊዜ የተለያዩ መርሀ-ግብሮችን ይከናውናሉ ተብለዋል፡፡