በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሚ/ር ሚ/ድኤታ ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ፣ ሚ/ር ሚ/ድኤታ ማዕረግ የመድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ፣ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የፓርቲ ኃላፊዎች፣ የካቢኔ አባላት፣ ባለሀብቶችና ነዋሪዎች ታድመዋል።
ለሰሜን እዝ መከላከያ ክብርና መስዋዕትነት በህሊና ጸሎትና ምርቃት የተጀመረው የድጋፍ ርክክቡ መርሃግብር የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በድሬዳዋ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየስ ተደርጓል።
ቆሞቀር የሆኑ ጁንታዎች ወደ መንበሩ ለመመለስ ጥረት የሚያደርጉት መቼም እንደማይሳካላቸው በመግለጽ የተጀመረው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ጅምር መሆኑንና እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የተደረገው አጠቃላይ የድጋፍ ሪፖርት በአስተዳደሩ ም/ከንቲባ አቶ ከዲር ጁሀር የቀረበ ሲሆን እስካሁን በአይነት 1ሚሊየን 760, ሺ ብር የሚገመት 36 የሀረር የበሬና 8 ግመል እንዲሁም 270 ሺ የሚያወጣ 100 ኩንታል አንደኛ ደረጃ የፉርኖ ዱቄት የተሰጠ ሲሆን በገንዘብ ጥሬ ብር ወደ ተዘጋጀ የባንክ አካውንት በአንድ ሳምንት የገባ 12 ሚሊየን ብር፣ ከከተማና ገጠር መንግስት አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ ና ነዋሪዎች ባለሀብቶች በአጠቃላይ ብር 14 ሚሊየን 87 ሺ ድጋፍ በተጨማሪም 843 ደም ዩኒት መለገስ ተችሏል።
በመርሃግብሩ መሠረት የተዘጋጀውን ድጋፍ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በቼክና በአይነት በማስረከብ የእለቱ የክብር እንግዳ የመከላከያ ሚ/ር ሚ/ድኤታዋ ክብርት ማርታ ሉዊጂ በምስጋና ንግግራቸው ”ደሜንና ጥሪቴን ለመከላከያዬ ብላችሁ በመደገፋችሁ ምስጋና አቀርባሁ” ብለዋል።
በመጨረሻም በኢትዮጵያ ህዝብ ብሄራዊ መዝሙር የእለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል ።


