የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በሁሉም ክልሎች እስከ ታህሳስ 30 ቀን እንደሚጠናቀቅ ትምህርት ሚኒስቴር ባሳወቀው መሰረት በድሬደዋ አስተዳደር ከታህሳስ አንድ እስከ ሦስት ፈተናው መሰጠት እንደሚጀመር ተገልፇል።
ይህን ተከትሎም የድሬደዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ በዛሬው እለት ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የስምንተኛ ክፍል ፈተና በአስተዳደሩ ለመፈተን የቅድመ ዝግጅት ስራው መጠናቀቁን በመግለፅ ከታህሳስ አንድ እስከ ሦስት ድረስ ፈተናው እንደሚሰጥ ገልፀዋል ፡፡
በአስተዳደሩ በገጠርና በከተማ የ2012 ዓ.ም በኮሺድ ምክንያት የስምንተኛ ክፍል ፈተና መፈተን ባለመቻሉ በዘንድሮ አመት እንዲፈተኑ በተወሰነው መሰረት 7113 ተማሪዎች የ45 ቀን የክለሳ ትምህርት ተሰቷቸው በ 90 ትምህርት ቤቶች 289 የመፈተኛ ክፍሎች ውስጥ በአንድ ክፍል 40 ተማሪዎች እንደሚፈተኑ ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
ፈተናው የ7ኛ ክፍል ሙሉ ይዘት እና የ 8 ኛ ክፍል የግማሽ አመቱን ይዘት እንደሚያጠቃልል የገለፁት የቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ ተማሪዎች በፈተናው ምንም አይነት መረበሽ እንደሌለባቸውም በመጠቆም ወላጆች ልጆቻቸውን ለፈተናው በበቂ ሁኔታ ዝግጁ እንዲሆኑ የስነ-ልቦና ምክር እንዲመክሩም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡


