የድሬዳዋ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አግልግሎት ነዋሪው የሚያገኘውን አገልግሎት ጥራት በማሻሻል የተገልጋዩን ቁጥር ለማሳደግ ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የተቋሙ ዲስትሪቢዩሽን ሲስተም ቴክኒካል ሰፖርት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ወ/ገብርኤል ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እንዳስረዱት በድሬዳዋ 45,000 (አርባ አምስት ሺህ) የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ያላቸው ህጋዊ ተገልጋዮች መኖራቸውን ጠቁመው ሌላው ነዋሪ በህገ-ወጥ መንገድ የመብራት ቆጣሪ ካላቸው ተገልጋዮች ላይ በቀጭን የኤሌክትሪክ ገመድ ኤሌክትሪክ በመሳብ ሲገለገል የቆየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ይህ ተግባር ህገ-ወጥ ከመሆኑ በዘለለ ለተለያዩ አደጋዎች በር ሲከፍት የቆየ መሆኑን አውስተው ይህንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ብሎም የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታትና የተደራሽነቱን መጠን ለማስፋት እያንዳንዱ አባወራ የራሱ የሆነ የመብራት ቆጣሪ እንዲኖረው ለማድረግ ከፍተኛ የቅድመ ዝግጅት ስራ በመስራት ወደተግባር መገባቱን ገልጸዋል፡፡
አቶ ግርማ አክለውም ቀደም ብሎ አዲስ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ለማስገባት ተቋሙ የሚጠይቃችው ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መሻሻያ በማድረግ ተገልጋዩ በሚቀርበው አገልግሎት በሚሰጥባቸው በሳቢያን ፣ በከዚራ፣ በኮኔል አልያም በመልካ ጀብዱ ቅርንጫፎች የይዞታ ማረጋገጫ ወይም ከሚኖርበት ቀበሌ የድጋፍ ደብዳቤ ይዞ መቅረብ ሳያስፈልግ የነዋሪነት መታወቂያ ብቻ በማቅረብ ፣ ተከራዮች ከአከራይ ጋር የገባውን የውል ስምምነት በማቅረብ እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብም የንግድ ፍቃዱን ይዞ በመቅረብ አገልግሎቱን በአጭር ቀናቶች ውስጥ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም ቴክኒካል ሰፖርት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ወ/ገብርኤል ከፍጆታ የክፍያ ስርዓቱ ጋር በተያያዘም ያለውን ሁኔታ ሲያብራሩ ቀደም ብሎ ሲሰራበት የነበረውን በቢል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ አሰባሰብ አሰራር ስርዓትን በማስቀረትና የፍጆታ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ቀደም ብሎ በተገልጋዩ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ከመቅረፍ በዘለለ የተገልጋዩን እንግልት ለመቅረፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በአሰራር ስርዓቱ ተገልጋዩ ባለ 12 ዲጂት የሆነውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ውል ቁጥር ይዞ በአቅራቢያው በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቅረብ የአገልግሎት ክፍያውን መፈጸም የሚችልበት አሰራር መዘርጋቱን እንዲሁም ከሂሳብ ተቀንሶ የሚፈጸም ክፍያና የቀጥተኛ ከሂሳብ ተቀናሽ አሰራር ስርዓት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በCBE Birr ፣ በኢንተተርኔት ባንኪንግ (Internet Banking) እና ሞባይል ባንኪንግ (Mobile Banking) አገልግሎት የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ መፈጸም የሚቻልበትን ስርዓት ተቋሙ መዘርጋቱን አመላክተዋል፡፡


