በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጽንሰ ሀሳብ፣ መርሆዎችና ጠቀሜታ ዙርያ ለኃይማኖት አባቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ተዘጋጀ

    የድሬዳዋ አስተዳደር የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጽ/ቤት በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በጥራትና ሁሉን ባሳተፈ መልኩ መስጠት እንዲችል በዘጠኙም የከተማ ቀበሌዎች ለሚገኙ ከተለያዩ እምነት ተቋማት ለተውጣጡ የኃይማኖት አባቶች በወሳኝ ኩነት ጽንሰ ሀሳብ ፣ መርሆዎችና ጠቀሜታ ዙርያ የሁለት ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተዘጋጀ፡፡
    በስልጠናው ላይ የፍትህ ፣ ጸጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብደላ በከር እንዳሉት ተቋሙ በዋናነት በሰው ህይወት ውስጥ የማይቀሩና የሚከሰቱ ኩነቶችን ልደት ፣ ጋብቻ ፣ ፍቺ ፣ ሞትና ጉዲፈቻን እየመዘገበ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
    ኃላፊው የወሳኝ ኩነቶች መመዝገብ ከሀገር ፣ ከማህበረሰብና ከግለሰብ አንጻር ኢኮኖሚያዊው ፣ ማህበራዊውና ፖለቲካዊ ፋይዳው ላቅ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም የእምነት ተቋማትም የወሳኝ ኩነቶች ከሆኑት ውስጥ በተለይም ለልደት ፣ ጋብቻና ሞት ማስረጃዎች የሚሰጡ በመሆኑ ከአስተዳደሩ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጽ/ቤት ጋር በተቀናጀና ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ ለመስራት እንዲቻል መድረኩ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የእምነት አባቶችም ከተቋሙ ጋር በአጋርነት በመስራት ለተሻለ ውጤት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡