በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የገጠር ቀበሌ የጤና ጣቢያ ኃላፊዎች ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

    በድሬዳዋ አስተዳደር የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት መጀመርን ተከትሎ በስተዳደሩ ገጠር ቀበሌ የሚገኙ የጤና ጣቢያ ኃላፊዎች የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ በተገኙበት ቁጥራቸው 5477 ለሆኑ ለገጠሩ ማህበረሰብ የጤና መድን ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የመግባያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
    በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ቢሮውን ወክለው የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት በገጠሩም ይሁን በከተማ መጀመሩ በሚኖረው የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የጤና ተቋማት ካለው የበለጠ አገልግሎትን ለማዘመን እንደሚረዳና የተሻለ ቅልጥፍናና ተጠያቂነት እንደሚያሰፍን ተናግረዋል፡፡
    በተያያዘም የጤና መድን አገልልገሎት የራሱን በጀት ይዞ በየጤና ተቋማቱ በመምጣቱ እስከ ዛሬ በነፃ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች በአስተዳደሩም ይሁን በሌሎች አካላት ሽፋን ስለተደረገና የጤና ተቋማቱን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ይህንን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
    ከነዚሁ የገጠሩ ክፍል የጤና መድን ተጠቃሚዎች መካከል 1757 የሚሆኑት በግላቸው የዓመታዊ ክፍያ 260 ብር የከፈሉና የተመዘገቡ ሲሆኑ ለቀሪዎቹ 3720 አባወራና እማወራዎች ደግሞ የገቢ ምንጫቸው ዝቅተኛ በመሆኑ የድሬዳዋ አስተዳደር ክፍያቸውን ሸፍኖላቸው ዓመቱን ሙሉ ከነ ቤተሰባቸው የህክምና አገልግሎቱን ምንም ወጪ ሳያወጡ የሚያገኙ እንደሆነ በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የምህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አስተባባሪ ሲ/ር ሜሪ አምዴ ተናግረዋል፡፡
    ሲ/ር ሜሪ አያይዘውም በቀጣይ በሚደረጉ የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በቁጥር ካሁኑ የተሻለ ተጠቃሚዎችን ወደ አገልግሎቱ ለማምጣት እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
    ምንጭ የድሬደዋ ጤና ቢሮ