የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በለገ-ኦዳ ጉኑን ፈታ ገጠር ቀበሌ ለሚገኙ ከ 320 በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች የሚውል የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ፡፡

    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በድሬዳዋ አስተዳደር ተከስቶ በነበረው የአንበጣ መንጋ ሳቢያ በሰብሎቻቸው እንዲሁም በግጦሽ ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው 320 በላይ የለገኦዳ ጉኑን ፈታ አርሶና አርብቶ አደሮች የሚውሉ ከ 160 ኩንታል በላይ የምግብ እህል ድጋፍ ተደርጓል፡፡
    በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ አርሶና አርብቶ አደሮች ድጋፎችን ከማድረግ በዘለለ በቀጣይ የህብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እንደሚሰሩም በድጋፍ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ወንድይፍራው ደጀኔ ተናግረዋል ፡፡
    ይህ በእንዲህ እንዳለም በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስጀመር በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ዩኒቨርሲቲ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ በላይ ተመራቂ ተማሪዎችን በመቀበል ላይ የሚገኝ ሲሆን ተማሪዎቹም ወደ ዩኒቨርሲቲው በሚገቡበት ጊዜም የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን የቅድመ ጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ ባደረገ መልኩ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን በመቀበል ላይ ይገኛል፡፡
    ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን እየተቀበለ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታን ለመከላከል ባወጣው መመሪያ መሰረት የተማሪዎች የመማሪያ፣ የመኝታና የመመገቢያ ክፍሎችን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አመቺ በሆነ መልኩ መዘጋጀቱን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መገርሳ ቃሲም ተናግረዋል፡፡
    የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታን ለመከላከል ከጤና ሚኒስቴር የሚወጡትን ህግና ደንቦችን በመከተል የጥንቃቄ ስራዎችን ከመስራት ጎን-ለጎን በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ይኖር ዘንድ ሰላም ቁልፍ ሚና እንዳለው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተናግረው በዩኒቨርሲቲው ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅትም ለሚመለከተው የፀጥታ አካላት በማሳወቅ አንድነታቸውን በማጠናከር ትምህርታቸውን ለመከታተል መዘጋጀታቸውንም ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታን መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ይኖር ዘንድ ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች ወደ ዩኒቨርሲቲው ለገቡ ተመራቂ ተማሪዎች በመስጠት ላይም ይገኛል፡፡