የጥላቻ አመለካከትን በማስወገድ ሀገራዊ አንድነትና ህብረ-ብሄራዊ ጥንካሬያችንን በማጉላት የተጀመረውን የእድገት፣ የልማት፣ የለውጥ ሂደቶች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ ሁሉም አካላት ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ።

    የኢትዮጲያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር በሰላም፣ በአብሮነት፣ በሀይማኖትና በብሄር ብዝሀነት አያያዝ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ የሀይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሆኑበት የምክክር መድረክ በሳምራት ሆቴል የተካሄደ ሲሆን በዚሁ መድረክ ላይም በክብር እንግድነት በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙሳ ጣሀ በሁሉም አካባቢዎች ሰላም ከማረጋገጥ አኳያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባና ለዚህም መሳካት የሀይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል ።
    የጥላቻ አመለካከትን በማስወገድ ሀገራዊ አንድነትና ህብረ-ብሄራዊ ጥንካሬያችንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጀመረውን የእድገት፣ የልማት፣ የለውጥ ሂደቶች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ ሁሉም አካላት ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የቅዱስ ፓትሪያሊክ ልዩ ፅህፈት ቤትና የውጪ ጉዳይ ግንኙነት ዋና ሀላፊና የድሬዳዋና የጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ-ፓፓስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ተናግረዋል ።
    የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ በሀገራችን ኢትዮጲያ ውስጥ በሚገኙ ከ 1610 በላይ ቅርንጫፎቹ ህብረተሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ከማገልገል ባለፈ በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ ሀገራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ የቢዝነስ ማናጀር አቶ ተካ ታደሰ ተናግረዋል ።