በድሬዳዋ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲን ወክለው ለፌደራል፣ ለከተማ አስተዳደርና ለቀበሌ ም/ቤት አባልነት የሚወዳደሩ እጩዎች ዝግጅት ማስፈጸሚያ እቅድ ዙሪያ ለ3ቱ ዘርፎች፣ ለከተማ ቀበሌና ለገጠር ክላስተር ፓርቲ አስተባባሪዎች ግንዛቤ ማስገንዘቢያ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የድሬዳዋ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየስ አሁን እየታየ ያለው የኮቪድ 19 ማሻቀብ አሳሳቢነት መልዕክት በማስተላለፍ ስለምርጫ ዝግጅት
ከቢሮ ኃላፊዎች፣ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና የም/ቤት ከፍተኛ አመራሮችና ቋሚ ኮሚቴዎች በተዘጋጀው እቅድ አላማ በቂ ዝግጅት እንዲደረግ አሳስበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲን ወክለው ለፌደራል፣ ለከተማ አስተዳደርና ለቀበሌ ም/ቤት አባልነት የሚወዳደሩ እጩዎች ዝግጅት ማስፈጸሚያ እቅድ በፓርቲው የፖለቲካ አቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይ የሚመረጡ እጩዎች በጥንቃቄ ስብጥር የጠበቀና መስፈርቱን ያሟሉ ሞጋች እጩ መፍጠር አለብን ብለዋል።
በማስፈጸሚያ እቅዱ በቀጣይ ለሚመረጡ እጩዎች 50% ሴቶች፣ 40% ወጣቶች እንዲሆኑና ለከተማ ምክር ቤት 60% ከከተማ እና 40% ከገጠር ስብጥሩን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበትና እጩዎች አመራረጥ ጥራት፣ ቁጥር፣ ህብረብሄራዊነትንና ስብጥሩን ከመጠበቅ አንጻር በጥንቃቄ መሰራት እንዳለበት ተገልጿል።
በመጨረሻም የአስተዳደሩ ም/ከንቲባ አቶ ከዲር ጁሀር ምርጫው ግልጽ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ እንዲሆን ከዚህ ቀደም የነበሩ ስህተቶች ሳይደገሙ የእጩ አመላመሉ በጥንቃቄ መሰራት እንዳለበት የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።


