ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 2/2013 ዓ.ም የ2012 ዓ/ም የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ሊሰጥ ነው፡፡

    የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት በአስተዳደሩ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የ2012 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል መሰናዶ ፈተና በኮቪድ-19 ምክንያት እንዲሁም በሀገር ደረጃ በኦንላይን(online) ፈተናውን ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ለፈተና ሊውሉ የነበሩት ታብሌቶች ከውጪ አለመግባታቸውን ተከትሎ ነው እስከ አሁን ፈተናውን ለመስጠት ያልተቻለው ብለዋል፡፡
    ወ/ሮ ሙሉካ አክለውም በአስተዳደራችን የ2012 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል የመሰናዶ ፈተና 1560 ተማሪዎች ለፈተና የሚቀመጡ ሲሆን ባሳለፍናቸው ሳምንታት በገጠርም በከተማው ያሉትን የዚህ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ለፈተና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በሞንታርቦ ጭምር ቅስቀሳና የኦሬንቴንሽን ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
    ከዚህም ጎን ለጎን በፈተናው ቀናት የፀጥታ ችግር እንዳይከሰት ከፀጥታ ሃይሎች ጋርም የዝግጅት ሥራዎች የተከናውኑ ሲሆን የተፈታኝ ተማሪዎቹ ወላጆችም የፈተናውን መሳካት፤ ተማሪዎቹን ለፈተና ከማዘጋጀት ጀምሮ የበኩላቸውን ትብብር እንዲያረጉ ጠይቀዋል፡፡
    የፈተናው ተፈታኝ ተማሪዎችም ምንም ዓይነት ፍረሃት ሳይሰማቸው ራሳቸውን ለፈተና እንዲያዘጋጁ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡