የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ በ2012 ዓ.ም በድህረና በቅድመ ምርቃት 728 ሴቶችና 1326 ወንድ በአጠቃላይ 2093 ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርአቱ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደተናገሩት ባለፉት ጥቂት አመታት ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በዩኒቨርስቲው አሳዛኝ የሆኑ ችግሮች ተፈጥረው የነበሩ ሲሆን በቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈፀሙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያቀፈ የማህበረሰብ አቀፍ አማካሪ ምክር ቤት ተመስርቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ኡባህ ከዚህም ጋር አያይዘው የ2012 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች ከኮቨድ -19 ጨምሮ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ የልፋታችውን ፍሬ ለማየት በመብቃታችሁ የእንኳን አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል ፡፡
የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ቦርድ ሰብሳቢና የፖለቲካ እና ሲቨክ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ደ/ር አለሙ ስሜ በበኩላቸው እንደተናገሩት በሀገራችን ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሆኑ የለውጥ ሂደቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች የሀገራችው ጉዳይ በትኩረት እንድትከታተሉና የሚጠበቅባችውን የዜግነት ሚና በመወጣት ለቀጣዩ ምርጫ ስኬታማነት የበኩላችውን እንድትወጡ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው 3.97 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ ተመራቂ ተማሪ ዩሴፍ ውቤ በሰጠው አስተያየት በትምህርት ዘመኑ የተለያዩ ችግሮችን በማለፍ ለዚህ በመብቃቱ መደሰቱን በመግለፅ በተማረው የትምህርት መስክ ሀገሩንና ማህበረሰቡን ለማገልገል የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርአቱ የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህና የሀይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በክብር እንግድነት ታድመዋል፡፡
በትዕግስት ቶሎሳ


