በግል የሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ጀምሮ መነሻቸውን ከጎሮ መናህሪያ አድርገው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡

    በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህዝብ ትራንስርትአገልግሎት አደረጃጀት ስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ነጋ እንደገለፁት የድሬዳዋ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 468/97 በተሠጠው ስልጣን መሠረት ማንኛውንም የግልም ሆነ የህዝብ ትራንስፖርት የመከታተል የመደገፍ፣ የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን እና ይህንኑ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ነው የገለፁት፡፡
    አቶ ተፈራ አክለውም እንደ ሃገር አቀፍ ለረጀም ጊዜ በህዝብ ትራንስፖርት የማታ ጉዞ የተነሳ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ለማስቀረት በሃገር አቀፍ ደረጃ የማታ ጉዞ እንዲቀር አቅጣጫ ተሰጥቶ የድ/ዳ/ት/ባ/ቅ/ጽ/ቤትም ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
    ሃገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት እየሠጠ ያለውን ቀልጣፋ ምቹ አገልግሎትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ከፍተኛ መሆኑን ተቋማችን ይረዳል ለዚህም በተገቢው መልኩ ዘርፉን ልንደገፍና ልናሳድግ እንደሚገባ እናምናልን ያሉት ዳይሬክተሩ ለዚህም እንደተቋም ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችለንን ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን ብለዋል፡፡
    አንድ እርምጃ ነው ያልነውን ሁሉም የግል አውቶቢሶች የሌሊት መነሻቸው ከአዲሱ የጎሮ መናህሪያ እንዲያደርጉ እና በቂ ጥበቃ ለአውቶቢሶቹ እንዲደረግ ምችችት ተደርጎ ተግባር ላይ ውሏል ነው ያሉት ፡፡ በዚህ አሰራር ተሳፋሪውም ሆነ ተሽከርካሪውን ከአደጋ ለመጠበቅ ታስቦ የተተገበረ አሰራር ነው ብለዋል ፡፡
    በመሆኑም ከየካቲት 30 2013 ጀምሮ ሁሉም የግል አውቶቢሶች መነሻ ከጎሮመናህሪያ መሆኑንና የመውጫ ሰአቱም ከማለዳው 11 ሰአት ላይ መሆኑን ነዋሪው ሊረዳ ይገባል ብለዋል፡፡
    ማህበራቱም በህጉ መሰረት እንዲንቀሳቀሱ ያሳሰቡት አቶ ተፈራ ይህን በማይከተሉት ላይ እንደተቋም እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡