የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን መስማት የተሳናቸዉ ዜጎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተጠቃሚ ለማድረግ በተዘጋጀዉ የአሰራር ማንዋል ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት አካሄደ ፡፡
የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ቱሉ እንደተናገሩት የዚህ ማንዋል መዘጋጀት ዋና አላማ መስማት ለተሳናቸዉ ሰዎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል አሰራር ስርዓት በመዘርጋትና ተግባራዊ በማድረግ ተሸከርካሪን በማሽከርከር ከቦታ ቦታ የመንቀስቀስና ሰርቶ የመኖር መብታቸዉ እንዲከበር ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት ግንዛቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ለማ በበኩላቸው ሀገራችን ኢትዮጽያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካል ጉዳታኞች መብት ኮንቬንሽን ከፈረሙ ሀገራት መካከል እንደምትገኝ በመግለጽ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ዜጎች ካላቸዉ ዕዉቀት ፣ ችሎታና ፍላጎት በመነሳት ያለምንም ገደብ ወይም ክልከላ በማንኛዉም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ መሆን እንዲችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል ፡፡ በዚህም መሰረት አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከቀረጥነጻ ተሸከርካሪ የማስገባት መብት እንደተሰጣቸዉ አክለዉ ተናግረዋል ፡፡
በማኑዋሉ ላይ እንደተገለጸው መስማት የተሳናቸዉ ሰዎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ለማግኘት በአዋጅ ቁጥር1074/2010 መሰረት ለየምድቡቹ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃና የማሽከርከር እድሜ ገደብ ፣ የጤና ምርመራ ዉጤት እና የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት አንደማንኛዉም ሰዉ ማሟላት አላባቸው፡፡
የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትም መስማት ለተሳናቸዉ የሚሰጠዉን ስልጣና የምልክት ቋንቋ በሚችል አሰልጣኝ ወይም አስተርጓሚ በመታገዝ የሚሰጥ ሲሆን የተግባር ስልጠናዉም አዉቶማቲክ ኮምፒዮን ወይም ማንዋል ባላቸዉ ተሸከርካሪዎች እንደሚሰጥ በወቅቱ ተገልጿል ፡፡
ከቀረበዉ ሰነድ በመነሳት ከተሳታፊዎች ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን መሰማት ለተሳናቸዉ ሰዎች የተዘጋጀዉ ማንዋል ከእንግሊዘኛ እና አማርኛ በተጨማሪ በምልክት ቋንቋም ጭምር ቢዘጋጅ የተሻለ ይሆናል ፣ መስማት የተሳናቸዉ ዜጎች እንደማንኛዉም ሰዉ የአሽከርካሪነት ሙያን እንደ አንድ የስራ አድል ቆጥረዉ ተቀጥረዉ መስራት እንዲችሉ እገዛ መደረግ አለበት የሚሉ እና ሰነዱ በመዘጋጀቱ የተሰማቸዉን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ባለስልጣን መስርያ ቤቱም ማንዋሉን በምልክት ቋንቋ ለማዘጋጀት ከኢትዮጽያ መስማት የተሳናቸዉ ብሔራዊ ማህበር ጋር እየሰራ እንደሚገኝ በወቅቱ ጠቁሟል፡፡
ምንጭ ፡-ከፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስተር


