የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የድሬዳዋ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ የአልባሳትና የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ አደረገ ።

    በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው የህግ ማስከበር ተልእኮ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት በድሬዳዋ በሚገኘው የምስራቅ እዝ ደረጃ 3 ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት እየተሰጣቸው ይገኛል ። የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮም ማርች 8 የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በህክምና ላይ ለሚገኙ የሰራዊቱ አባላት የሚሆን የአልባሳትና የንፅህና መጠበቂያ እቃዎችን ድጋፍ አድርገዋል ።
    በድጋፍ ስነ-ስርአቱ ላይም በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ\ሮ ከሪማ አሊ የዘንድሮውን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ሴቶች በፖለቲካ መስክ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ሴቶችን ከማበረታታት አንፃር ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን ወ\ሮ ከሪማ ገልፀው ይህንኑ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግም ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል ።
    ድጋፍ እንደ ቢሮ ብቻ ሳይሆን እንደ አስተዳደርም በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን መሆናቸውን እንደሚገልፁም የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሆኑት ወ\ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ተናግረዋል ።
    የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተደረገው ድጋፍ በነበረው የህግ ማስከበር ተልእኮ ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊቱ አባላት ከፍተኛ የሆነ ብርታት እንደሚሆን የምስራቅ እዝ ደረጃ 3 ሆስፒታል የሴቶች ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት ሌተናል ኮረኔል እታለም መኩሪያ ተናግረው ለተደረገላቸውም ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።