የአለም የሴቶች ቀን ማርች 8 ከየካቲት 21 ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች በአስተዳደራችን እየተከበረ ነው፡፡ ከእነዚህ ዝግጅቶች መካከል በአስተዳደሩ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ አዘጋጅነት “የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበረሰብ አንገንባ” በሚል መሪ ቃል ሴት አመራሮች የተሳተፉበት የቶክ ሾው መድረክ ተካሄደዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ለ110ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮ የአለም ሴቶች ቀን በተለይም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ማህበረሰቡ እንዲያወግዝ የሴቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ ትኩረት ተሰቶ ይከበራል፡፡
በቶክ ሾው መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ከሪማ አሊ የዘንድሮውን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ሴቶች በፖለቲካ መስክ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ የውሳኔ ሰጪነት ክፍተቶችን ለመፈታት መጠነ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል ፡፡ አክሎም ወ/ሮ ከሪማ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ሴቶችን ከማበረታታት አንፃር ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በቶክ ሾው ዝግጅቱ ላይ የክብር እንግዳ የነበሩት የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ በበኩላቸው ሴቶች በግለሰብ ደረጀ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ብቁ ከሆኑ ለቤተሰቦቻቸውና ለሀገራቸው የሚያበረክቱት አሰተዋጾ ከፍተኛ ይሆናል ብለዋል፡፡ ሴቶች በአመራርነት የሚሳተፉበትን የፋይናንስ ሂደቶችን በብቃት እንደሚወጡ በጥናቶች የተረጋገጠ በመሆኑ ይህም ለሀገር ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ለማየት ተችሏል ብለዋል ወ/ሮ ፈጡም ፡፡
በቶክ ሾው ላይም ሴቶችን በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መስክ ለማብቃት ምን መስራት እንዳለበት ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የተሰራ የጥናት ፅሁፍ የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት መምህርት መቅደስ ሀይሉ አቅርበዋል፡፡


