የድሬዳዋ ዩንቨርስቲ ሳምንታዊ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በዘጠኙም የከተማ ቀበሌዎች ለማካሄድ መዘጋጀቱ ተገለጸ::

    የድሬዳዋ ዩንቨርሲት የዩንቨርሲቲውን ማህበረሰብ ተሳታፊ ያደረገ ወርሃዊ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
    በዛሬው እለት የ2ተኛ ዙር ፕሮግራሙንም በዩንቨርሲቲው በዋናው በር መግቢያ አካባቢ አካሂዷል፡፡ በአካል ብቃት እንቅስቃሴው የዩንቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ፣ መምህራንና ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
    የአካል ብቃት እንቅስቃሴው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ የተሰጠውን ትኩረት መነሻ ማድረጉን በድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡ ዩንቨርሲቲው እንቅስቃሴውን ለማስጀመር 10 የሚሆኑ የዩንቨርሲቲው አባላትን ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ስልጠና እንዲያገኙ በማመቻቸት በዩንቨርሲቲው ማህበረሰብና በከተማው ነዋሪው ላይ መነቃቃትን ለመፍጠር እንዲቻል በየወሩ በመደበኛነት በርካታ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴው እየተካሄደ ስለመሆኑ ገልጸዋል ፡፡
    በቀጣይ በቋሚነት በዩንቨርሲቲው አካባቢ እየተካሄደ ያለውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማስፋት በዘጠኙም የከተማ ቀበሌዎች በየሳምንቱ የሚካሄድ ስለመሆኑ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡ በእንቅስቃሴውም የሚጠበቀው ውጤት እንዲመዘገብም ከድሬዳዋ አስተዳደር፣ ከዘጠኙም ቀበሌዎችን ከወጣትና የተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡አክለውም ህብረተሰቡ የራሱን ጤና ለመጠበቅም በአካባቢው ላይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ባህሉ እንዲያደረግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
    የዩንቨርሲቲው የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የአካል ብቃት እንቅስቃሴው አስተባባሪ የሆኑት አቶ ማንደፍሮ ዳኘው እንዳሉትም ሁሉም አካል ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖር ያለምንም ወጪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በአካባቢው ላይ ቢያደርግ ጤናውን መጠበቅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
    በዩንቨርሲቲው አስተባባሪነት እየተደረገ የሚገኘው የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ዩንቨርሲቲው ከቆመለት አላማ አንዱ ከሆነው የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ውስጥ የሚካተት መሆኑን የተናገሩ ሲሆን በስራውም ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ያስችላልም ብለዋል፡፡ በቀጣይም ከዩንቨርሲቲው ማህበረሰብ በዘለለ የከተማውን ህብረተሰብ ያሳተፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለመጀመር ጥናት አድርገን አጠናቀናልም ብለዋል፡፡