የድሬዳዋ ከተማ በ2009 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑ 11 ከተሞች ውስጥ አንዷ ነች፡፡ ፕሮግራሙ በአስተዳደሩ በሚገኙ 9 የከተማ ቀበሌዎች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ የቀበሌ 04 አስተዳደርም በሁለተኛ ዙር በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ ወንድ 199 ሴት 635 በድምሩ 834 የቀበሌው ነዋሪዎችን በድሬዳዋ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አዳራሽ አስመርቋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ማርቆስ ባዩህ የከተማ ምግብ ዋስትና በአስተዳደራችን መተግበሩ ለተጠቃሚዎች መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የአጭር ጊዜ የምግብ አቅርቦት ችግርን ለማቃለል አስችሏል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ፕሮግራሙ ዜጎችን በቀጣይ ከከፋ ድህነትና ከተመጣጠነ ምግብ እጦት ችግር በራሳቸው ጥረት ደረጃ በደረጃ በማላቀቅ ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲቋቋሙና የተሻለ ኑሮ እንዲመሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል በማለት ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በደረቅ ቆሻሻ ማሰባሰብና ማስወገድ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ስራዎች ላይ ተሰማርተው አካባቢያቸውን ከመጥቀማቸው በተጨማሪም በሚከፈላቸው ክፍያ ኑሮዋቸውን እንዲያሻሽሉና ጥሪት እንዲያፈሩ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑት አካላት ላለፉት 3 ዓመታት ከሚያገኙት ገቢ በቆጠቡት 20% ተቀማጭ ብር ላይ በመንግስትና በዓለም ባንክ የተወሰነውን ተጨማሪ ድጋፍ ለእያንዳንዳቸው ብር 17,878 (አስራ ሰባት ሺህ ስምንት መቶ ሰባ ስምንት ብር) በአጭር ጊዜ ውስጥ በመስጠት ወደዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ስራ እንዲሸጋገሩ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡ ተመራቂዎቹ ለቀጣይ ስራቸው እንዲረዳቸውም የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡


