የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአቤቱታዎች አቀራረብ፣ በውሳኔ አሰጣጥ፣ አፈፃፀምና ጥራት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንደሚፈታ የታመነበት ተቋማዊ ሪፎርም እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
የህገ መንግስት የበላይነት፣ ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነት፣ ውጤታማ የሀብት ክፍፍል እና ተቋማዊ የማስፈፀም አቅም የተቋሙ የሪፎርም ትኩረቶች መሆናቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ ከክልል አፈጉባኤዎች፣ ከጠቅላይ አቃቢ ህግ እና ከህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ እንዲሁም ከፍርድ ቤቶች ተወካዮች ጋር እየመከረ ነው።
በዚህ ውይይት በአቤቱታዎች አቀራረብ፣ በውሳኔ አሰጣጥ፣ አፈፃፀምና ጥራት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንደሚፈታ የታመነበት ተቋማዊ የሪፎርም ጥናት ላይ ግብአቶች ይገኙበታል ተብሏል።
ለውይይት መነሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁራን እየቀረበ ባለው የሪፎርም ጥናት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያልተሻገራቸው ችግሮች ተነስተዋል።
በተለይም የውሳኔዎች መዘግየት፣ የፖለቲካ ጣልጋ ገብነት፣ የህገ መንግስታዊ ትርጉም ውሳኔዎች የጥራት ችግርና ሁሉንም የሚያስማማ አለመሆን የምክር ቤቱ ችግሮች መሆናቸው ተነስቷል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ተቋማዊ ለውጥ ያስፈለገው በምክር ቤቱ አሰራር ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል።
ህገ መንግስታዊነትና ህገ መንግስታዊ የበላይነትን ለማስፈን ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በተሟሏ መልኩ ለመወጣት ሪፎርም ማድረግ ማስፈለጉም ነው በመድረኩ የተገለጸው።
ምንጭ፦EBC


