በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ አራት የገጠር ክላስተር የሚገኙ ከ 1150 በላይ የሚሊሻ አባላት የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት ተመረቁ ።

    በድሬዳዋ አስተዳደር 6 ተኛው ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ በአስተዳደሩ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳቸው ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች አካሂደዋል ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የፊታችን ሰኞ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊና ያለምንም የፀጥታ ችግር ምርጫው ተጀምሮ ይጠናቀቅ ዘንድ በተለይም በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ አራት የገጠር ክላስተር ለሚገኙ ከ 1150 በላይ የሚሊሻ አባላት የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት ከመመረቃቸውም ባለፈ በሁሉም የገጠር ክላስተሮች ለሚገኙ የሚሊሻ አባላትም አዲስ የደንብ ልብስ ተሰፍቶላቸዋል ።
    ከዚህ ቀደም ለሚሻ አባላቱ በአንድ ማእከል ይሰጥ የነበረው ስልጠና አሁን ላይ ሀገራዊ ምርጫው ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ የሚሊሻ አባላቱ አጠቃላይ የፀጥታ ስራዎችን መጠበቅ ስላለባቸው ስልጠናውንም በየክላስተሩ እንደተከታተሉና ይህንንም ስልጠና የቢሮው ከፍተኛ አመራሮችና የፖሊስ አባላት በየክላስተሩ በመሄድ መስጠታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሙሳ ጠሀ ተናግረው ለሚሊሻ አባላቱ ስልጠና ከመስጠት ጎን-ለጎንም ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረውን የደንብ ልብስ በተሻለ የደንብ ልብስ በመቀየር የሚሊሻ አባላቱ አሁን ላይ በሞራልም ሆነ በአካል ብቃትም ቢሆን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና 6 ተኛውም ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር ይካሄድ ዘንድ ከአስተዳደሩ ፖሊስ ጋር በጋራ በመቀናጀት ለመስራት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውንም ነው አቶ ሙሳ ጠሀ የተናገሩት።
    6 ተኛው ሀገራዊ ምርጫ በድሬዳዋ አስተዳደር ባሉ አራቱም ክላስተር ስራ ያሉ 38 ቱም ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር ሰላማዊ በሆነ አግባብ ለማካሄድ ይቻል ዘንድ 1150 የሚሊሻ አባላት የአጭር ጊዜ ስልጠና እንደወሰዱና ከነዚህም ውስጥ በዋሂል ክላስተር ስር በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ስር ያሉ 240 የሚሆኑ ሚሊሻዎችን በማሰልጠን ብቁ ማድረግ መቻሉን የድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ምክትል ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ አብደላ በከር ተናግረው በቀጠይም የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ አኳያ ነዋሪው ህብረተሰብ ከሚሊሻ አባላት ጋር በጋራ በመሆን ሊሰሩ እንደሚገባም አቶ አብደላ ተናግረዋል ።
    በወሰዱት ስልጠና መሰረት በምርጫው ወቅት የሚያጋጥሙ ማንኛውንም የፀጥታ ችግሮች በመፍታት ምርጫው ሰላማዊ በሆነ አግባብ እንዲካሄድ የራሳቸውን አስተዋፆ እንደሚወጡም የአጭር ጊዜ ስልጠናውን ወስደው ያጠናቀቁ የሚሊሻ አባላት ተናግረዋል ።