ወጣቶች በሀገራቸው ዘላቂ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ሰላምን ከማይፈልጉ ሀይሎች ጋር ባለመተባበርና ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላማቸውን ማስጠበቅ እንደሚገባ ተገለፀ ።

    የ 2012 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይ ተሳታፊ ለሆኑ ወጣቶችና ተቋማት የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራም በድሬዳዋ አስተዳደር ተካሂዷል ።
    በድሬዳዋ አስተዳደር በየአመቱ በሚካሄደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይ በአስተዳደሩ በሚገኙ በከተማም ሆነ በገጠር የህብረተሰቡን ችግሮች ሊፈቱና ሊያግዙ የሚችሉ ዘርፈ-ብዙ የማህበራዊ አገልግሎት ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን በ 2012 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታን የመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ፣ ችግኝ ተከላና ጥበቃ ፣ ደም ልገሳ ፣ የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት ፣ የመንገድ ደህንነት ፣ የአካባቢዎች ፅዳትና ውበት ስራዎች ተሰርተዋል ።
    ከዚሁ ጋር ተያይዞም በ 2012 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይ ተሳታፊ ለሆኑ ወጣቶችና ተቋማት የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራም ተካሂዷል ።
    በዚሁም መርሀ-ግብር ላይም በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ለተሳታፊዎች የሚሰጠው ስነ-ልቦናዊ እርካታ ልምድ ከመለዋወጥና ከመተሳሰብ ብሎም አብሮነትን ከማዳበርና ከማህበራዊ መስተጋብር አኳያ የሚፈጥረው እድል እንዲሁም ለሚደረግለት ሰው የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ተናግረው ይህም ብዙዎችን ወጣቶች የበለጠ ለመልካምነት የሚያበረታና የወጣቱን የመልካም ተግባር ለሀገር ልማት ማዋል እንደሚቻል የሚያሳዩበት መሆኑንም አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
    ምክትል ከንቲባው አክለውም በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የተሳተፍ ወጣቶች ፣ ያስተባበሩ ቀበሌዎች ፣ የአስተዳደሩ ወጣቶችን ስፖርት ኮሚሽን ፣ የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች ፣ ላደረጉት አስተዋፆ ምስጋቸውን አቅርበው ወጣቶች በተለይም በሀገራቸው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሰላምን ከማይፈልጉ ሀይሎች ጋር ባለመተባበርና ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላማቸውን ማስጠበቅ ዋንኛ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባም አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
    በዚሁ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ 35 ሺህ 126 የሚሆኑ ወጣቶችና በጎ-ፍቃደኞች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን ከ 31 ሚሊዮን 921 ሺህ 143 ብር የሚገመት አስተዋፆ መደረጉን የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ ተናግረው ከአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ላይም በአፈር ጥበቃና በፅዳት 14 ሺህ 380 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ተሳታፊ መሆናቸውንም ነው አቶ ሻኪር አህመድ የተናገሩት ።
    በወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራም ላይም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብርም በኢትዮ-ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ጊቢ ውስጥ አካሂደዋል ።