ዕድሜው ከ18 እስከ 20 ዓመት የሚገመተው ወጣት አስረስ ነገዬ በድሬዳዋ ከተማ ሎተሪ በማዞር ኑሮውን ይመራል።
ደንበኞቹን ባለዕድል ለማድረግ የሚተጋውን ወጣት የኢዜአ ሪፖርተር በአገሩ ጉዳይ ሲያነጋገግረው የሰጠው መልስ የግሉን ብቻ አልነበረም። ”እኔና 40 ዎቹ” ብሎ የጓደኞቹንም አቋም የሚያንጸባርቅ ነበር።
”እኔና 40 ጓደኞቼ ወደ ግንባር ለመዝመት ተዘጋጅተናል!”ያለው በተመሳሳይ ሙያ የሚባትሉትን ጓደኞቹን ወክሎም ነው። በአገር ጉዳይ የማይዛነፍ አቋም እንዳላቸው ስለሚያውቅ።
”ሰላም ከሌለ ሠርቶ መነገድና መኖር ከባድ ነው፤ አገር ሰላም እንዳትሆን ሽብርተኛና ጦርነት እየፈጠረ የሚገኘውን ቡድን እንዋጋለን” በማለት በሎተሪ አዟሪነት ለሁለት ዓመታት የሰራው ወጣት ይናገራል። ጓደኞቹ የተለየ አቋም እንደሌላቸው በማከል።
በሳቢያን ቀበሌ ወጣቶች በበጎ ተግባሩ የሚታወቀው ነፃነት ጥላሁን ትህነግን የሚታገለው፤ በፍቅርና በአንድነት የመኖር ተምሳሌት የነበራትን ድሬዳዋን በማድቀቅና መገለጫዋን በማሳጣቱ እንደሆነ ይናገራል።
”የድሬዳዋ ሕዝብ መተዳደሪያ የነበሩትን የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካና የቀድሞውን የምድር ባቡር ድርጅት በመናድ የነዋሪውን ኑሮ አናግቷል” ይላል፡፡
ለአገር ሉዓላዊነት መረጋገጥና ትህነግን ለመደምሰስ ድጋፍ ማድረጋችን እንቀጥላለን ያለው ደግሞ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደም የለገሰው ወጣት ፍፁም አብርሃም ነው፡፡
”ለአገር ደሙን ለሚያፈሰው ሠራዊት ደም ከመለገስ ባሻገር፤ ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፌ ሕይወቴን ለአገሬ እሰጣለሁ” ሲል ለመስዋዕትነት መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡
መከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ሰሞኑን የዘመቱትን ለመቀላቀል ወስኛለሁ ያለው ደግሞ ወጣት ፋሲል ሃይሉ ነው፡፡
የትግራይ ወጣት ከአገሩ ጎን በመቆም አገር አፍራሹን ትህነግ እንዲያወግዝና እንዲታገልም ጠይቋል፡፡
ሌላው ወጣት ሳላሃዲን ሹካር በበኩሉ ”በየሥፍራው ተደብቀው የሚገኙ የሽብርተኛውን ቡድን ተላላኪዎች ለሕግ ለማቅረብና ሰላም በመጠበቅ ኃላፊነቴን እወጣለሁ” ብሏል፡፡
በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት በድሬዳዋም ብሎም በአገር ደረጃ እየተፈጠረ ያለውን ህብረትና አንድነት መጠናከሩንም ገልጿል።
ምንጭ: ኢዜአ


