ሀገር የማዳን ጥሪ ተቀብለው <<ሀገራችን ሀብታችን፤ሀብታችን ለሀገራችን >>በሚል መሪ ቃል የአስተዳደሩ ባለሀብቶች ላደረጉት ድጋፍ በአስተዳደሩ የእውቅናና የምስጋና መረሀ ግብር በዛሬው እለት ተካሄዶል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ በመረሀ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ህውሓት አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ አገዛዙን ጭኖ በቆየባቸው ባለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት እንዳይኖረው በመከፋፈልና እርስ በርስ እንዲጋጭ በማድረግ የቆየው አሸባሪ ቡድኑ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማችን ነዋሪዎች የኑሮ መሠረት የነበሩትን ምድር ባቡርና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካን የመሰሉ የድሬዳዋ መለያ የነበሩና ወሳኝ የኢኮኖሚ ድርሻ የነበራቸውን ተቋማት በመዝረፍና በማዳከም የፈፀመውን ተግባር እንዲሁም በአጠቃላይ በድሬዳዋ ላይ የተሰራውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሸፍጥ ከቶውን ቢሆን የማይዘነገ ነው ብለዋል።
ከንቲባ አህመድ ቡህ አክለውም ለሚናፈሱ ፕሮፖጋንዳዎች ጆሮ ባለመስጠት፣ የኢኮኖሚ አሻጥሩን በማክሸፍና ለአገር አንድነት ዘመቻው ያለንን ያለስስት በመስጠት ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ደጀን በመሆን የኢትዮጵያን ህልውና የማስቀጠል የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ከባለሀብቶች 22.4 ሚሊየን መሰብሰቡን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሜቴ ሰብሳቢ አቶ ከድር ጆሀር ገልፀዋል።
ምክትል ከንቲባው አክለውም ከአስተዳደሩ ከመንግስት ሠራተኞች 5% እስከ 50% ከደመወዛቸው መሰብሰቡን እንዲሁም ከከተማና ከገጠር ነዋሪዎችም በስንቅ፣ በአይነት እና በአገልግሎት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የደጀንነት ድጋፍ እየተደረገ ነውም ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ላደረጉ ባለሀብቶችና ድርጅቶች በድጋፋቸው ልክ የሰርተፊኬትና የዋንጫ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በመርሀ ግብሩ የተሳተፉ ባለሀብቶች ሀገራቸውን ለማዳን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።


