የከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ የአዲስ አመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት፦

    በቅድሚያ ለመላው የኢትዮጲያ ሕዝብና ለድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች እንኳን ለ2014 አዲስ አመት በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ፤ አዲሱ አመት የሠላም ፣ የጤና ፣ የፍቅርና የአንድነት እንዲሆንላችሁ በራሴና በድሬዳዋ አስተዳደር ስም መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ።
    💛አዲስ ዓመት ባለፈው አመት ወደኋላ የጎተቱንን ያረጁ አስተሳሰቦች ጥለን አዲስ ብርሀን ለማየት አዲስ ተስፋ የምንሰንቅበት፤ በአዲስ መንፈስ ያቀድናቸውን አዳዲስ ሀሳቦችና እቅዶች ለመፈፀም ከራሳችን ጋር ቃልኪዳን የምናስርበት ልዩ ጊዜ ነው።
    💛የምንገኝበት ጊዜ በሀገራችን የተጀመረውን አዲስ የለውጥ ጉዞ ለመቀልበስ የውስጥና የወጪ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው በአገር ህልውና ላይ አደጋ የደቀኑበት በመሆኑ አዲሱ አመት የውስጥ ልዩነታችንን ወደ ጎን አድርገን የተደቀነብንን የህልውና አደጋ በአንድነት ለመመከት ቃል የምንገባበት ሊሆን ይገባል፡፡
    💛አዲሱ ዓመት የገጠሙንን ፈተናዎች በጥበብና በማስተዋል ተሻግረን የአገራችንን አንድነትና የሕዝባችንን ወንድማማችነት በፅኑ መሠረት ላይ በመገንባት የበለፀገችና ለነዋሪዎቿ የምትመች ድሬዳዋን እውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንሰራበት ሊሆን ይገባል፡፡
    💛በአዲስ አመት ግለሰቦች ብቻ
    ሳይሆኑ ተቋማትም አዳዲስ ስራዎችን፣ ቴክኖሎጂዎችን ፣ የአሰራር ስርዓቶችን ለመተግበር ያቅዳሉ፤ የቀደመ ስራቸውን አሻሽለው በአዲስ መንገድ ለመከወንም አዲስ አሰራርና አካሄድ ይጀምራሉ።
    💛ስለሆነም በተሳካ ሁኔታ በተካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ መሠረት በአዲሱ አመት
    ከሚመሰረተው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የሚመረጡ
    አዳዲስ የአስተዳደሩ አመራሮች ተቋማትን ለማጠናከር፣ የድሬዳዋን ልማት ለማፋጠንና የነዋሪዎችን እርካታ የሚፈጥር አገልግሎት ለመስጠት በከፍተኛ ሁኔታ ጥረት እንደሚያደርጉ እተማመናለሁ።
    💛በመጨረሻም ለመላው የድሬዳዋ ነዋሪዎች እንዲሁም በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ለምትኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና የድሬዳዋ ወዳጆች ለሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ድሬዳዋ ልማትና እድገቷ እንዲፋጠን በምትችሉት ሁሉ እንድትሳተፉና አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ ጥሪ እያቀረብኩ ፤ አዲሱ አመት በክፋት ስራ የተጠመዱ የአገራችን ጠላቶች ተወግደው ሠላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና ወንድማማችነት በኢትዮጵያ ምድር የሚሰፍንበት እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ።
    መልካም እንቁጣጣሽ !!
    አመሠግናለሁ !!
    🇪🇹 🇪🇹 🇪🇹
    ድሬዳዋ ከንቲባ ፅ/ቤት